በይቅርታ የታደሰ ህይወት - ኢዜአ አማርኛ
በይቅርታ የታደሰ ህይወት

ወጣት ዘውዱ ማሞ ትውልድና እድገቱ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ዛሮታ ቀበሌ ነው።
በስራው ስኬታማ ለመሆንና ኑሮውን ለማሸነፍ ሁሌም የሚተጋው ዘውዱ ከእለታት አንድ ቀን የተወሰኑ ግለሰቦች ያለበት ድረስ በመሄድ ያልሆነውን ሆኗል ወደፊት ደግሞ እንዲህ ይሆናል እያሉ አሉባልታ በማውራት የተሳሳተ መንገድ እንዲከተል ሊያሳምኑት ሞከሩ።
ለመልእክተኞቹም ሰርቶ ለመለወጥ፣ ቤተሰቦቹን ለማገዝና በአካባቢው የልማት አጋር፣ የሰላም ቀናኢ መሆን እንጂ እነርሱ የሚሉትን መንገድ እንደማይመርጥ ደጋግሞ ነገራቸው።
የሚደጋገም ነገር በሰዎች አዕምሮ ላይ ጫና እና ጥርጣሬ መፍጠሩ አይቀርምና በምልልስ ሃሳባችንን ተቀበል የሚሉት ሰዎች ምን እያሉኝ ነው፣ ምንስ ፈልገው ነው የሚለውን ጉዳይ ማሰላሰሉ አልቀረም።
የጋዝጊብላው ወጣት ቆይቶም በመልእክተኞቹ የጥፋት አጀንዳ መሸነፉ አልቀረም፤ እሽታውን ገልፆላቸው ህዳር 2016 ዓ.ም ጠመንጃ አንግቶ ተከትሏቸው ጫካ ገባ።
የጫካ ህይወትንም አንድ ብሎ በመጀመር በአካባቢው የጥፋት አጀንዳ ይዘው ከተነሱት ጋር እርሱም ተቀላቅሎ ጥፋትን የዘወትር ስራው አደረገው።
ከዚህ የጥፋት ቡድን ጋር በጫካ እየተሹለከለከ የአካባቢውን ነዋሪ እየዘረፈ፣ እየበደለና እየገደለ መዝለቅ ለምን? የሚለው ጥያቄ ግን በአዕምሮው ያቃጭልበት ይዟል።
በዚህ ሂደት ከጥፋት ቡድኑ የሚላቀቅበትንና የሚወጣበትን መንገድ እያሰበ ከቆየ በኋላ ተሳክቶለት መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ትጥቁን በመፍታት ቤተሰቦቹን ዳግም ተቀላቅሏል።
በራስ ህዝብና በቤተሰብ ላይ በመሸፈት መግደል፣ መዝረፍና ማገት ለምን? የሚለው ዘውዱ፤ እኔ ባጠፋሁት ሁሉ ይቅርታ ጠይቄ ተመልሻለሁ፤ ሁላችሁም ተመለሱ በማለት መልእክቱን አስተላልፏል።
በጥፋቱ በመፀፀት ሕብረተሰቡን ለመካስ ቃል በመግባት የልማት አርበኛ የሰላም አምባሳደር በመሆን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጦ፤ በይቅርታ የታደሰው የዘውዱ ህይወቱ ቀጥሏል።
አሁን የተለያዩ የግብርና ስራዎች ላይ ተጠምዶ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና እያለ ያለው ዘውዱ በተጓዳኝ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ጥገና እና ሌሎችንም ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል።
የትጥቅ እንቅስቃሴ ለማንም ቢሆን ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው በተግባር አይቻለሁ የሚለው ዘውዱ የሰላም አማራጭ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን አንስቷል።
በመሆኑም ሰላም በመንግስት ጥረት ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ ሁሉም የሰላም አምባሳደርና የልማት አርበኛ መሆን ይኖርበታል ሲል አንስቷል።
የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ፤ የዘውዱ መልካም ተግባር በጥፋት መንገድ ላይ ያሉ ሁሉ ከተግባራቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ከነበረበት የተሳሳተ መንገድ ወጥቶ አሁን ላይ በልማት ከፊት የሚሰለፍ፣ ለሰላምና መረጋጋት የሚተጋ የሰላም አምባሳደር ሆኗል ብለዋል።
አጠቃላይ ሕብረተሰቡንና የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈ የሰላምና የፀጥታ ስራ በመከናወኑ በጥፋት መንገድ ላይ የነበሩ ታጣቂዎች እየተመለሱ መሆኑን ገልጸው ሌሎችም የተሰጠውን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ፤ ከሃገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመቀናጀት በተከናወነው ስራ በቅርቡ ብቻ 336 የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪ ተቀብለው መግባታቸውን ተናግረዋል።
በተሳሳተ መንገድ ጫካ ገብተው ያልተመለሱ ቀሪ ታጣቂዎችም የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው በአፋጣኝ እንዲመለሱ አሁንም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።