አፍሪካውያን ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህ የሚጠይቁበት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካውያን ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ፍትህ የሚጠይቁበት ጉባኤ

አፍሪካ የምንኖርባትን አለም ህልውና የሚያስጠብቅ እና የሚያስቀጥል ጠንካራ ኃይል ያላት አህጉር ናት ማለት ይቻላል።
ከአማዞን ቀጥሎ ሁለተኛው የምድራችን ሳንባ እየተባለ የሚጠራው የኮንጎ ተፋሰስ በዚሁ አህጉር የሚገኝ ነው። ተፋሰሱ በርካታ ካርቦን ዳይኦክሳይድ አምቆ በመያዝ የአየር ንብረት ሚዛንን ይጠብቃል።
እንደ አባይ፣ ኮንጎ እና ኒጀር የመሳሰሉ ወንዞች ከአፍሪካ ድንበር ተሻግረው በግብርና እና የስነ ምህዳር ጥበቃ ላይ እየተወጡት ያለው ሚና ትልቅ ነው።
ከተንጣለለው የሳቫና የሳር መሬት እስከ ከርሰ ምድር የተፈጥሮ ጸጋዎች የአፍሪካ ብዝሃ ህይወት የዓለም ስነ ምህዳር በዘላቂነት እንዲቀጥሉ እያደረጉ ይገኛል።
አፍሪካ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል ምንጭ በዓለም ንጹህ የኢነርጂ ኃይልን ለማስፋት ያለው ሚና ጉልህ መሆኑ አያጠራጥርም።
አህጉሪቷ ዓለምን በተፈጥሯዊ ሀብቷ እየጠበቀች ቢሆንም እምብዛም ድርሻ በሌላት የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ሆናለች። ተከታታይ ድርቅ እና ጎርፍ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ማጣት ከቀውሶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
የኢንዱስትሪ ዘመን አሃዱ ብሎ ከጀመረበት እ.አ.አ 1850ዎቹ አንስቶ ዓለም ላይ ከሚለቀቀው ካርቦን ዳይኦክሳይድ አፍሪካ ያላት ድርሻ ከ3 እስከ 4 በመቶ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአንጻሩ የበለጸጉ ሀገራት በዓለም ለይ በካይ ጋዝን በመልቀቅ 80 በመቶ የሚሆን ድርሻ አላቸው።
እነዚህ የበለጸጉ ሀገሮች እ.አ.አ በ2009 በዴንማርክ ኮፐንሃገን 15ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ -15) ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ለሆኑ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ቢገቡም ቃል ኪዳናቸውን እየጠበቁ አይደለም።
ለአፍሪካ አህጉር ጨምሮ ለሌሎች በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ያደጉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲያሟሉ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛል።
አየር ንብረት ለውጥ ፈተና ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት አፍሪካዊያንን ለዚህ አንገብጋቢ አጀንዳ በጋራ የሚያቆም ሁነት ከፊት ለፊታችን እየመጣ ነው።
ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ የሚያዘጋጁት ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአህጉሪቷ መዲና አዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው የአፍሪካ መሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ኢኖቬተሮች እና ለውጥ ፈጣሪዎች በአንድ ጥላ ስር የዘመኑ ትልቅ ፈተና በሆነው የአየር ንብረት ቀውስ እና መፍትሄው ላይ ይመክራሉ።
ችግሩ አለ ብሎ ከማውራት ባለፈ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያለ ሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችም ይቀርባሉ።
ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ፍትህ ሊሰጠን ይገባል የሚል ጠንካራ እና የጋራ ድምጽ የሚያሰሙበት ነው።
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስፈልጋትን ፋይናንስ የበለጸጉ ሀገራት እንዲሰጡም ጠንካራ ጥሪ ይቀርብበታል ተብሎ ይጠበቃል።
30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) በመጪው ህዳር ወር 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤለም ከተማ ይካሄዳል።
አፍሪካውያን በኮፕ 30 ላይ አህጉሪቷ ሊኖራት የሚገቡ አጀንዳዎችን እና የጋራ አቋሞችን ያዘጋጃሉ።በጉባኤው ከአዲስ አበባ የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ድምጽ ጎልቶ ይሰማል።
ዓለም የሚቀርበውን ጥሪ ጆሮ ሰጥቶ በማዳመጥ በአየር ንብረት ለውጥ የተግባር ምላሽ እንደሚሰጥም ይጠበቃል።