ሳይንስና ቴክኖሎጂ
የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ቋሚ ኮሚቴው
Jan 22, 2025 53
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፡- የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል። ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ታሳቢ በማድረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነትን ሊያጎለብትና ሊያዘምን እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል። ቋሚ ኮሚቴው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።   የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) የተቋሙን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን የቋሚ ኮሚቴ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። መንግስት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎችን፣ መመሪያዎችን እና ስታንዳርዶችን በማዘጋጀት ተግባራዊ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም ከተሽከርካሪ መቀመጫ ቀበቶ አጠቃቀም፣ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ መግጠምና ማስተዳደር፣ የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን ተደራሽነት ለማስፋት መናኸሪያዎችንና ደረቅ ወደብን ለአገልግሎት ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። በአብነትም የሞጆ ደረቅ ወደብን ለማስፋፋት እየተሰራ ያለውን ስራ አንስተው በአሁኑ ሰዓት የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 80 በመቶ አካባቢ መድረሱን ጠቁመዋል።   እንደ ሀገር በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለህብረተሰቡ የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት አቅም እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል። የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የነዳጅ ድጎማው በታለመለት አላማ መሰረት በምን መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ጠይቀዋል። መንግስት በአለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመር በዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ጫና መቅረፍ የሚያስችል ስራ ሲሰራ መቆየቱንና ይሀም ተጠናክሮ መቀጠሉን ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል። እንዲሁም ተገቢ ባልሆነ መልኩ የነዳጅ ድጎማን በሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ ተጠያቂነት ለማስፈን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን(ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ እና የዘመነ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ እና ሊጠናከሩ የሚገቡ መሆኑን አመላክተዋል። በቀጣይም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን ማዘመን የሚያስችሉ ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የማሰልጠኛ ተቋማትን አሰራር መፈተሽ እና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አቅም ማሳደግ እንዳለበትም የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበዋል።
የአዳማ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተሻለ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ልምድ የሚወሰድበት ነው - የሸገር ከተማ አመራር አባላት
Jan 22, 2025 49
አዳማ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፡- በአዳማ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጠን የሚያሳልጠው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ማዕከሉን የጎበኙ የሸገር ከተማ አመራር አባላት ገለጹ። የሸገር ከተማ የየሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራር አባላት የአዳማ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሂደትና እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ከተሳተፉ አመራር አባላት መካከል የሸገር ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ መኮንን አምቤ ለኢዜአ እንደገለፁት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር ጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው። በዚህም በሸገር ከተማ አስተዳደር ሰባት የሚሆኑ የእለት ተእለት አገልግሎት የሚበዛባቸውን መስሪያ ቤቶች በአንድ ማዕከል ማደራጀት የሚቻልበትን ልምድ ማግኘታቸውን እንስተዋል። በጉብኝቱም ለተገልጋዮች የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት ተገልጋዮች ጊዜና ገንዘባቸውን የሚቆጥቡበት አሰራር መዘርጋት እንደሚቻል መገንዘባቸውን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የህብረተሰቡ የአገልግሎት እርካታ ግብረ መልስን ዲጂታላይዝ ማድረጉ ለሚሰጠው አገልግሎት ግብረ መልስን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። የሸገር ከተማ የኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ኢንጂነር ገልማ ገመሮ በበኩላቸው የአዳማ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተሟላ ቴክኖሎጂ ተደግፎ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ልምድ የወሰዱበት መሆኑን አንስተዋል። በተለይ ተገልጋዩን ከእንግልት፣ ከጊዜ ብክነት፣ ከወጪና ብልሹ አሰራር የሚያፀዳ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን መመልከታቸውን ተናግረዋል። አገልግሎት አሰጣጡ ህዝቡ በመንግስት ላይ የሚኖረውን አመኔታ የሚያሳድግ ነው ያሉት ሃላፊው ያገኙትን ተሞክሮ በሸገር ከተማ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የአዳማ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ በሪሶ ዶሪ በበኩላቸው በከተማው የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎች በጥናት በመለየት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል። በዚህም ሁሉም አገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቶች አንድ ቦታ ሆነው በፍትሃዊነትና በግልፀኝነት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸው በዚህም የከተማው ነዋሪ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞችና የከተማ አስተዳደር ሴክተር ተቋማትን በዲጂታል አገልግሎት በማገናኘት በሁሉም የአስተዳደር እርከን የተሳለጠ አገልግሎት የመስጠት ስራ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።
ለአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣን የመዳረሻ ቪዛ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል
Jan 22, 2025 50
  አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ህብረት ጉባዔን ለመታደም ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ። የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመጪው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለእንግዶች አገልግሎቱን የሚሰጡ 124 ባለሙያዎች የዲፕሎማቲክ ፕሮቶኮል፣ የቱሪዝምና ማርኬቲንግን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውን ተናግረዋል። ይህም ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ብቁና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠትና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ያግዛል ብለዋል። ከሰው ሃይል ስልጠናው ባለፈ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና በአግባቡ መምራት የሚቻልበት ሁኔታ መዘርጋቱንም አንስተዋል። ከተለያዩ አገራት ህጋዊ ፓስፖርት ይዘው ለሚመጡ እንግዶች የመዳረሻ ቪዛ (Visa on Arrival) ለመስጠት የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል። አገልግሎቱ በተያዘው ጥር ወር የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ለመጀመር አቅዶ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር ዋና ዳይሬከተሯ አስታውሰዋል። በዚህ መሰረት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የኢ-ፓስፖርት ቡክሌቶች ተመርተው ከውጭ መግባታቸውንና የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ስልጠና መጠናቀቁንም አመልክተዋል። ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ለ10 ዓመታት የሚያገለግለው ኢ-ፓስፖርት አገልግሎት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የዲጅታል ሽግግሩ ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግና አካታች ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል ነው - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
Jan 21, 2025 63
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ዘመናዊ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግና አካታች ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡ በኢንተርኔት ሶሳይቲ የተሰናዳውና በኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሰረተ ልማትን ማሳደግ ላይ ያተኮረው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡   የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ በዲጅታል 2025 ስትራቴጂ መሰረት የዲጅታል ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰዋል። የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፋችና እያዘመነች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የ4 ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት ሀገራዊ ሽፋን 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተዋል። 5 ጂ ኔትወርክም በትላልቅ ከተሞች አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፥ ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ነው ያሉት። ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው ቴሌ ብር ከ51 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት አካታች የዲጅታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮችና የዳታ ማዕከል አቅራቢዎች በሀገሪቱ እንዲሰማሩ በማድረግ ዲጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አሻራቸውንን እያሳረፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጅታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ አገልግሎትና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትና በአፍሪካ የዲጅታል አብዮት መሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል። ለሦስት ቀናት የሚቆየው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።   የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንዳሉት፤ የኢንተርኔት ጉባኤ በኢጋድ አባል አገራት የኢንተርኔት ተግዳሮቶችን መፍታት፤ የእውቀት ሽግግር፤ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የበይነ መረብ ትስስርን ማጎልበትን ያለመ ነው። የኢንተርኔት ልማት ላይ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ቁልፍ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሄዎች መስጠት እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡   የኢንተርኔት ሶሳይቲ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አስራት ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢንተርኔት የፈጠራ አቅም እንዲጎለብት ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ድህነትን ለማስወገድና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማሳካት ለኢንተርኔት መሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መስጠቷንም ነው የጠቆሙት፡፡    
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት 70 በመቶ ደንበኞቹ ገንዘብ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያንቀሳቀሱ መሆኑን ገለጸ
Jan 21, 2025 71
መቀሌ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ዲስትሪክት 70 በመቶ ደንበኞቹ ገንዘብ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እያንቀሳቀሱ መሆኑን አስታውቋል። የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ልሳነወርቅ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባንኩ የሞባይል ባንኪንግን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ አማራጮችን ዘርግቶ በማስተዋወቁ በርካታ ደንበኞቹን የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል። በዲስትሪክቱ በሚገኙ 58 ቅርንጫፎች ስር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ኤልያስ፤ ከእነዚህ መካከልም 70 በመቶ ያህሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ገንዘባቸውን እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህም ገንዘብን ደህንነቱ በተጠቀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል። እንዲሁም ፈጣን የግብይት አገልግሎትን በመፍጠር ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም ያስቻለ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በተጨማሪም ደንበኞች ባሉበት ሆነው ሌሎች ስራዎቻቸውን እያከናወኑ ገንዘብ ለማስተላለፍም ሆነ የተለያዩ ክፍያዎችን ለመፈፀም ቴክኖሎጂው እየረዳቸው መሆኑን አቶ ኤልያስ አመልክተዋል። በቀጣዮቹ ወራትም የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚ ያልሆኑ ደንበኞቹን ስለ አገልግሎቱ ያላቸውን ግንዛቤ ለማዳበር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ለማካሄድ እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል። የባንኩ የረጅም ጊዜ ደንበኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መሀሪ ፍስሀ፣ ባንኩ የጀመረው የዲጂታል አገልግሎት የገንዘብ ዝውውር ጤናማነትን ስለሚያረጋግጥ መልካም መሆኑን ገልጸዋል። አገልግሎቱ ፈጣንና አስተማማኝ በመሆኑም ስራቸውን እንዳቀለለላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላው የባንኩ ደንበኛ አቶ አሰፋ ገብረ ስላሴ ናቸው።
ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
Jan 21, 2025 64
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ተደራሽነት እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ። ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ መክፈቻ መርሐ ግብር ላይ ነው። ኢንተርኔት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለማህበራዊ ትስስርና ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው፥ ለቀጣናዊ ትብብርና ለፈጠራ ማደግ ምቹ ምህዳር የሚፈጥር ነውም ብለዋል። ሆኖም በቀጣናው ካለው ፍላጎት አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት አሁንም ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል። ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ መሰረት የዲጂታል ሽግግርን እውን የሚያደርጉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰዋል።   የቴሌኮም መሰረተ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፋችና እያዘመነች መሆኑን ገልጸው የ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽነት ሀገራዊ ሽፋን 34 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን አንስተዋል። 5ጂ ኔትወርክም በትላልቅ ከተሞች አገልግሎት መጀመሩንና ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ተጠቃሚነትን ያሳድጋል ነው ያሉት። ኢትዮ ቴሌኮም የጀመረው ቴሌ ብር ከ51 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራት አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮችና የዳታ ማዕከል አቅራቢዎች በሀገሪቱ እንዲሰማሩ በማድረግ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ሽግግር ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ አገልግሎትና አካታች ኢኮኖሚን ለመገንባትና በአፍሪካ የዲጂታል አብዮት መሪ እንድትሆን የሚያስችል ነው ብለዋል። ለሦስት ቀናት የሚቆየው የኢንተርኔት ልማት ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በሌሎች የኢጋድ አባል ሀገራት የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ይበልጥ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ በሐሰተኛ መረጃና ማንነት አገልግሎት ለማግኘት የሚደረግ ሙከራ እንዲቀንስ እያደረገ ነው
Jan 21, 2025 57
አዲስ አበባ፤ጥር13/2017(ኢዜአ)፦የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ሐሰተኛ መረጃና ማንነት ተጠቅመው ህገ ወጥ አገልግሎት ለማግኘት የሚደረጉ ሙከራዎችን ለመከላከል እያስቻለ መሆኑን የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ። የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐሚድ ኪኒሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ከፍተኛ መብትና ጥቅምን የሚይዙ ሰነዶችን የማረጋገጥ፣ የማዋዋልና ደኅንነቱን የመጠበቅ አገልግሎት እያከናወነ ይገኛል። የተቋሙ አሰራር ተገማች፣ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀና ተዓማኒነት ያለው ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዙ በርካታ የማሻሻያ ስራዎችን ማከናወኑ ውጤታማ እያደረገው ነው። በዚህም ከተቋሙ የሚወጡ ሰነዶች ተመሳስለው የማይሰሩና በቴክኖሎጂ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ለ776 ሺህ ዜጎች አገልግሎት መሰጠቱንም ተናግረዋል። በዚህም ከተቋማት ጋር የቴክኖሎጂ ትስስር በመፍጠር የማጭበርበር ሙከራዎችን መከላከል መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ በተለይም የፋይናንስ ተቋማት፣ከመሬት ልማት፣ ከአሽከርካሪ፤ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ከወሳኝ ኩነት ምዝገባና የዜግነት አገልግሎትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የመኪና ሽያጭ፣ የባንክ ብድር ውል፣ ውክልና፣ የንግድ ማኅበራት መዝገባና ቃለ ጉባኤ መያዝ፣ ቃለ መሃላ፣ ከጋብቻ በፊት ያለ ንብረት ሥምምነትና የተረጋገጡ ዶክመቶችን ለባለመብቶች በሚሰጥበት ወቅት የማረጋገጥ ተግባር መከናወኑን አብራርተዋል። ከወሳኝ ኩነት ምዝገባና የዜግነት አገልግሎት ጋር በመታወቂያ፣ በጋብቻ ሰርተፍኬት፣ በልደትና መሰል አገልገሎቶች የመረጃ ማጣራትና የመመዝገብ ስራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከፓስፖርት፣ መንጃ ፈቃድ፣ የጋብቻ ሰርተፊኬትና ከሌሎች መረጃዎች ጋር በተገናኘ 201 ሐሰተኛ ሰነዶች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ በአስገዳጅነት ተግባራዊ መደረጉ በሐሰተኛ ሰነድ ለመጠቀም የሚደረጉ ሙከራዎች እንዲቀነሱ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመቀናጀት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም በዲጂታል ማህተም፣የሚታተሙ ሰነዶችን በኤሌክትሮኖክስ ማረጋገጥ የሚያስችል ሚስጥራዊ ህትመት መጀመሩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ትብብር በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ከክልሎች ጋርም እንዲሁ በመረጃ ቋት ትስስር በመፍጠር በጋራ መሥራት የሚያስችሉ ስረዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል። አገልግሎት ፈላጊ ዜጎች ትክክልኛ ሰነዶችን ብቻ በመያዝ የተፋጠነ አገልግሎት ማግኘነት እንደሚችሉ ገልጸው፥ በሀሰተኛ ሰነድ ለመጠቀም መሞከር በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።  
የፋይዳ መታወቂያ የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት ትግበራን ለማፋጠን ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
Jan 20, 2025 69
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2017(ኢዜአ)፦ የፋይዳ መታወቂያ የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት ስራን ውጤታማ ለማድረግ ምቹ መደላድል መፍጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ። የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በአውደ ጥናቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።   የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን ገልጸዋል። አዲስ የተቀረጸው የዲጂታል መንግስት ስትራቴጂ አካል በሆነው የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት አማካኝነት በትግበራ ላይ የሚገኘው ፋይዳ መታወቂያ ዘርፉን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል። የቶኒ ብሌር ከፍተኛ አማካሪ እና የህንድ ኤሌክትሮኒክ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ኢንተርፕረነርሺፕ ሚኒስትር ራጂቭ ቻንድራሴክሃር ህንድ በዲጂታል መሰረተ ልማት ያስመዘገበችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጤት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። ስትራቴጂካዊ እቅዶችን በመተግበር የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን የማልማት ስራ ስኬት መመዝገቡን አመልክተዋል። የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማለዳ ብስራት ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ ለመንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አቶ አደም ፋራህ በአዳማ ከተማ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመውን "ጋዲሳ ኦዳ" ጎበኙ
Jan 20, 2025 62
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2017(ኢዜአ)፦ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ "ጋዲሳ ኦዳ" የተሰኘውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጎበኙ። አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት በዛሬው ዕለት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአዳማ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በተናበበና በተቀናጀ መልኩ በአንድ ማዕከል ለመስጠት የተቋቋመውና "ጋዲሳ ኦዳ" የሚል ስያሜ የተሰጠውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ጎብኝዋል። አሰራር ስርዓቱ 29 ሴክተሮችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ በቴክኖሎጂ በተደገፈ አግባብ ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለው ስርዓት የባለጉዳዮችን እንግልት የቀነሰ፣ ገቢን ለመሰብሰብ ምቹ የሆነ፣ ልማዳዊ የሆነውን የወረቀት ስርዓት ከ80 ፐርሰንት በላይ በሁሉም ሴክተሮች ውስጥ ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል።   ይህም የአሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ከፍተኛ እድል የፈጠረ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት። የከተማ አስተዳደሩ በከተማ ደረጃ ያሉ ተቋማትን በአንድ ማዕከል ከማሰበሰብ ባሻገር የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ተቋማትም በአንድ ማዕከል እንዲሰሩ ማድረጉ እጅግ የሚበረታታ እና ለሌሎች ከተማ አስተዳደሮችም ተሞክሮ የሚሆን ነውም ብለዋል። በከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አመታት በተሰሩ ስራዎች መሬትን ሙሉ ለሙሉ በካድስተር ቴክኖሎጂ ዲጅታል ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ በከተማዋ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተዘረጋው የሲሲቲቪ ካሜራ ዝርጋታ ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል። በቀጣይም በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በምርጥ ተሞክሮነት ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግ እንደ ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለወጣቶችና ሕጻናት ምቹ የዲጂታላይዜሽን ምህዳር እየተፈጠረ ነው - ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) 
Jan 18, 2025 78
  አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2017(ኢዜአ)፡- መንግሥት ወጣቶችና ሕጻናት በቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ቁልፍ ተዋናይ የሚሆኑበት ምቹ ምህዳር እየፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና ውድድር ማዕከል ጋር በመተባበር በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሲያሰለጥናቸው ለነበሩ ተማሪዎች የዕውቅና ሰጥቷል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) መንግስት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች በማሰልጠን ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን ጉዞ ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ምቹ ምህዳር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም በርካታ ወጣቶች በተለያዩ ዓለማት በቴክኖሎጂና በፈጠራ ተወዳዳሪ ሆነው ሀገራቸውን ማስጠራት ጀምረዋል ነው ያሉት። መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው፤ የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል። የኢትዮ ሮቦ ሮበቲክስ መስራችና ዋና ስራ አስከያጅ ሰናክሪም መኮንን ስልጠናው ወጣቶች የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ አተገባበርን በመማር ሮቦትን እንዲቀርጹ የሚያደርግና በሮቦት ኮዲንግና እና ፕሮግራሚንግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።   ዕውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች ከዚህ ቀደም በሮቦቲከስ ፕሮግራሚንግና ኢንጅነሪንግ ሰልጥነው በቻይና ሀገር በተካሄደ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ውድድር ላይ በመሳተፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የሜዳሊያና የዋንጫ ተሸላሚ የነበሩ እንደሆኑ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ክፍተትን ለማጥበብ እየተጋ ይገኛል 
Jan 17, 2025 85
  አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ክፍተትን ለማጥበብ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተጋ እንደሚገኝ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኩዋይኖርና የባንኩ የምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሊያንድር ባሶሌ(ዶ/ር) ከተመራ ከፍተኛ ልዑክ ጋር በአፍሪካ የዲጂታል መጻኢ እድገት ዙሪያ ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ኢትዮ ቴሌኮም ከአፍሪካ ግዙፉ የቴሌኮም ኦፕሬተር እንደመሆኑ የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት ክፍተትን ለማጥበብ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ አካታችና ቀጣይነት ያለው እድገትን ለማምጣት እየተጋ እንደሚገኝ አብራርተዋል። አክለውም አፍሪካ ያሉባትን ተግዳሮቶች ለማለፍ፣ አዳዲስ ዕድሎችንና ዘላቂ ልማትን ለመፍጠር ቴክኖሎጂን እና ዲጂታል መፍትሔዎችን መጠቀም እንዳለባትም አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ ዘርፈ ብዙ ጥረት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ከማሳካት ባለፈ የአፍሪካ ዲጂታል አቅምን ለማጎልበት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን በፋይናንስ መደገፍ ከትስስር ባሻገር አጠቃላይ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚ ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም የሀገራችንን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ፋይናንሰሮችን ጨምሮ ቁልፍ ዓለም አቀፍ አጋሮችን በመሳብ የበለጸገች ዲጂታል አፍሪካን ራዕይ እውን የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኩዋይኖር የኢትዮ ቴሌኮምን ፈጣን ዕድገትና ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እየተጫወተ ስለሚገኘው አስተዋፅኦ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በአጋርነት ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን ጉዳዮች በማብራራት የአፍሪካ ልማት ባንክ የኩባንያውን ዲጂታል ኢኒሸቲቭ ለመደገፍ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
አዲስ ያስገባናቸው ድሮኖች ከከተማ ፀጥታ ቁጥጥር ባሻገር የቦርደር ሴኪዩሪቲን የኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቀላሉ መቆጣጠር የምንችልበትን ዕድል ይፈጥራሉ - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
Jan 16, 2025 108
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፡- አዲስ ያስገባናቸው ድሮኖች ከከተማ ፀጥታ ቁጥጥር ባሻገር የቦርደር ሴኪዩሪቲን የኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በቀላሉ መቆጣጠር የምንችልበትን ዕድል ይፈጥርልናል ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ።   ኮሚሽነር ጀነራሉ በዋናው መስሪያ ቤት የተደራጀውን የድሮን ፓይለት ማሰልጠኛ ማዕከል(UAV Simulation Training Center) መርቀው ስራ አስጀምረዋል፡፡ በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ጀነራሉ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ፖሊስ ውስጥ የተዋወቀው የድሮን ቴክኖሎጂ ማዕከል ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮቻችን የቴክኖሎጂ ስልጠና አግኝተው በፖሊስ ውስጥ የተሻለ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት የተፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል። አሁን ላይ በተቋሙ ያለው የድሮን አቅም በፖሊስ የወንጀል መከላከል ሰርቪላንስ እና የምርመራ ስራ ከፍተኛ እገዛ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡   በፖሊስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊስ በዘመኑ እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎችን ታጥቆ አያውቅም ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሪፎርሙ አሁን ላይ ከአፍሪካ አምስቱ ምርጥ የፖሊስ ተቋማት ውስጥ ለመግባት እያደረገ ያለውን ጥረት በሚያግዝና ለአፍሪካ ወንድሞቻችንም ልምድ እና ተሞክሮ ማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ እየተደራጀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በሪፎርሙ መንግስት ለፖሊስ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የሀገራችን ፖሊስ ዘመናዊ ትጥቆች እንዲኖሩትና ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ የወንጀል መከላከል ስራዎቻችንን ለመስራት በሚያስችል አቅሙን እያሳደገ ነው ብለዋል፡፡   እንደአዲስ አበባ ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ፓትሮል ለማድረግ የእግረኛ ፖሊስ ሠራዊትን ከድሮን ፓትሮል ጋር በማቀናጀት እና በማዋሀድ የወንጀል መከላከል ስራችንን እያቀላጠፍን የምንሰራበት እድል ከመፍጠር ባለፈ አድማዎች ሲያጋጥሙ በተደራጀና በጠንካራ ሠራዊታችንና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን በቀላሉ ችግሮችን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ነው ያሉት፡፡ እንደ አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ያሉ መድረኮች ሲኖሩ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችን ዘግቶ ቪአይፒዎችን ማስተናገድ የሚያስችል የራሱ የሆነ ኮማንድ ኮንትሮል ያለው ዘመናዊ Road block ተሸከርካሪም በዛሬው ዕለት ተመርቆ ስራ እንዲጀምር መደረጉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኤሌክትሮኒክ ቲኬት የመናኸሪያ አገልግሎት አሰጣጥን ምቹና ቀልጣፋ አድርጓል
Jan 16, 2025 91
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦ በሀዋሳ ከተማ መናኸሪያዎች የተተገበረው ኤሌክትሮኒክ ቲኬት የመናኸሪያ አገልግሎት አሰጣጥን ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን ማስቻሉን የሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሐዋሳ ከተማ መናኸሪያዎች አገልግሎትን ለማዘመን የተተገበሩ ዘመናዊ አሰራሮችን ተመልክተዋል። የሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ታፌ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የመናኸሪያዎችን ደረጃ የማሻሻልና በቴክኖሎጂ የማስደገፍ ሥራ እየተከናወነ ነው። የመናኸሪያዎችን የትኬት አገልግሎት ፈጣን፣ ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ የኤሌክትሮኒክ ወይም ኢ-ትኬት ሥርዓት መተግበሩን ጠቅሰዋል። ይህም ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ትርፍ መጫን፣ ከተመደቡበት የስምሪት መሥመር ውጪ መጫንና መሰል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መቅረፉን ገልጸዋል። በቀጣይም ከሐዋሳ ከተማ ተሞክሮን በክልሉ ዞኖች እና ወረዳዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Jan 16, 2025 105
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2017(ኢዜአ)፦ ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የርዕደ መሬት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጁነታችንና የምላሽ ሁኔታችን ባለን ቴክኖሎጂ፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ትንተናና የትንበያ አቅም የሚወሰን ነው ብለዋል።   በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ የስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዛሬ ዛሬ በተደረገው ጉብኝት በርዕደ መሬት ነክ ሳይንሳዊ ምርምር አበረታች ስራዎች ለመመልከት መቻሉን ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በርዕደ መሬት ክስተት ዙሪያ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ተጠናከረ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።   አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የሳይንሳዊ ትንተና እና ትንበያ ቡድኖችን በማደራጀት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ዝግጁነትን ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ተቋማት ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ኃይል ጠንካራ ቁመና እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ተቋማቱ በችግር ፈቺ የፈጠራ ምርቶች ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል?
Jan 15, 2025 77
የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ግብ ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ስራዎችን ዕውን ማድረግ ነው። ዘርፉ የኢንዱስትሪላይዜሽን ጉዞ መስፈንጠሪያ ነው። በተለይም የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚያስቀሩ ሀገራዊ ተኪ ምርቶችን በማምረት። በዚህም ተቋማቱ አንድም በምርምርና ፈጠራ ስራዎችን ውጤታማ መሆን፣ አንድም በዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ብቁና በቂ የሰው ኃይል የማፍራት ግብ ሰንቀው ይሰራሉ። ተቋማቱ የፈጠራ ውጤቶችን በተግባር ከማዋል በዘለለ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ረገድም አይተኬ ሚና ይጫወታሉ። በኢትዮጵያም ይህ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት በርካታ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ተቋቁመው ወደስራ ገብተዋል። ለመሆኑ ተቋማቱ በችግር ፈቺ የፈጠራ ምርቶች ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል የሚለውን ኢዜአ የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን ለአብነት ቃኝቷል። የኮሌጁ መምህር ወርቁ ፈንታሁን እና ተማሪ ዳግም ጋርጦ ኮሌጁ እና የኮሌጁ ሰልጣኞች ቁልፍ ግባቸው ችግር ፈቺነት ነው ብለው ያምናሉ። መምህሩና ደቀ መዝሙሩም በቅርብ የተመለከቱትን ችግር የሚፈታ የፈጠራ ስራ ለማውጣት ወሰነው ወደስራ ገብተዋል። መምህር ወርቁ ከሩቅ ሳይሆን ከቅርብ ችግር ተነስተው የእንስሳት መኖ ማቀነባበርያ ማሽን መስራት ችለዋል። ይሄውም በሚያስተምሩበት የጀኔራል ዊንጌት ኮሌጅ የሚካሄደውን የከብት እርባታና ማድለብ ስራ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የመኖ እጥረት የመኖ ማቀነባበሪያ ለማምረት ምክንያት ሆኗቸዋል። ፈጠራቸውም የኮሌጁን ችግር አቃሏል። ይኼውም ኮሌጁ ለእንስሳት መኖ ግዢ የሚያወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረታቸው ነው። መምህር ወርቁ እንደሚሉት ማሽኑ ከውጭ ቢገባ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚጠይቅ ሲሆን እርሳቸው ግን በ400 ሺህ ብር ብቻ ሀገር ውስጥ መተካት ችለዋል። ማሽናቸው በሰዓት 4 ኩንታል፤ በቀን ደግሞ 15 ኩንታል መኖ ያቀነባበራል። ከአዋጭነት አኳያም በወር እስከ 100 ሺህ ብር ትርፍ ያስገኛል ይላሉ። የመኖ ማቀነባበርያ ማሽኑን በብዛት አምርቶ በአዲስ አበባ በከተማ ግብርና ለተሰማሩ አካላት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ። የኮሌጁ ተማሪ ዳግም ጋርጦ ደግሞ አካል ጉዳተኞችን፣ አቅመ ደካሞችንና ህፃናትን መመገብ የሚያስችል ሮቦት ነው የሰራው። ሮቦቱ ለአንድ ሰው በቀን የሚመገበውን ምግብ እና የሚጠጣውን ውሃ በልኬት በተሰጠው መጠን ልክ ድጋፍ ለሚሹ ህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችላል። ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ መስራት ለሀገር ያለውን ወሳኝ ፋይዳ የሚያነሳው ዳግም፤ ለዚህ ደግሞ ለዘርፉ ምቹ ምህዳር ሊፈጠር እንደሚገባ ያነሳል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ የቴክኖሎጂና የኢንተርፕራይዝ ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ልጋኔ እንደሚሉት በከተማዋ በሚገኙ 15 የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ለማፍራት ተተኩሯል። ማሰልጠኛ ተቋማት ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ስራዎችን በማውጣት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ እንደሆነም ይገልጻሉ። እስካሁንም ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ጥሬ ግብዓቶች በመጠቀም ተኪ ምርቶችን በማምረት ምሳሌ የሆኑ ኮሌጆች እንዳሉ የጀኔራል ዊንጌትን ለአብነት ይጠቅሳሉ።
አገልግሎቱ አሰራሩን ይበልጥ ለማዘመን ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው -ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት
Jan 14, 2025 87
አዲስ አበባ፤ጥር 6/2017(ኢዜአ)፦የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አሰራሮቹን ይበልጥ ለማዘመን ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል። ዋና ዳይሬክተሯ፥ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ልዑክ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል። ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ወቅትም ተቋሙ በሪፎርም ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀው፥ የሚሰጡ አገልግሎቶች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማደራጀት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ስራዎችንም ለማዘመን ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ አካላት ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይበልጥ ቀልጣፋ ከማድረግ አኳያ ልዑኩ ያለውን ልምድና ተሞክሮ በሚያጋራበት እንዲሁም በጋራ ሊሰሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት በበኩላቸው፥ ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ በትብብር ለመስራት ፋላጐት እንዳላቸው መግለጻቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ ቴሌኮምና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ''ስማርት ኮርት ሲስተም" ን ለመተግበር የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
Jan 14, 2025 94
ባህርዳር፤ ጥር 6/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮ ቴሌኮምና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ"ስማርት ኮርት ሲስተም" ን በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው ናቸው። ''ስማርት ኮርት ሲስተም" የክስ መዝገቦች አያያዝን ማሻሻል፣ በቪዲዮ የተደገፈ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ፋይል እንዲከፍቱ ዕድል የሚፈጥር መሆኑና ሌሎች የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሻሻል ስርዓት መሆኑ ተመልክቷል።   የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ መንግስታዊ አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑን የሚመጥን ዲጅታል ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ የሚልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ''ዛሬ የፍትህ ስርዓትን በቴክኖሎጂ አግዘን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር የጋራ ስምምነት በማድረጋችን ደስ ብሎኛል'' ብለዋል። ''የተጣለብንን ኃላፊነት በብቃትና በጥራት ለመወጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን'' ሲሉ ተናግረው ኩባኒያው በየተቋማቱ ለዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመን አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ በክልሉ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ለማሻሻል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ፍርድ ቤቶች ስራቸውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው ካልሰሩ አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ እንደማይቻል ገልፀው፤ የዳኝነትና የፍትህ ስርዓቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለዚህም በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር የተቀላጠፈ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ''የስማርት ኮርት'' አገልግሎት በተለይ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ፋይል እንዲከፍቱ ትልቅ ዕድልን ይዞ የሚመጣ ከመሆኑም በላይ የተቀላጠፈ የዳኝነት አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይም የኢትዮ ቴሌኮምና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአመራር አባላት ተገኝተዋል።  
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶቹ ሪች ዲጂታል በኢትዮጵያ የአይሲቲ ዘርፍ መዋዕለ ንዋዩን የማፍሰስ ፍላጎት እንዳለው ገለጸ
Jan 13, 2025 95
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፡-የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ተቋም ሪች ዲጂታል (REACH Digital) በኢትዮጵያ በዘርፉ መዋዕለ ንዋዩን የማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ገሰሰ (ዶ/ር) ከሪች ዲጂታል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት ኮሚሽነሩ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ጨምሮ ኢትዮጵያ በተለያዩ ቁልፍ ዘርፎች ያላትን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የግሉ ዘርፍ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሪፎርሞችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የአይሲቲውን ዘርፍ የሚያሳድጉ ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፎች መኖራቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ፖሊሲው መንግስት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትምንት ለመሳብ እየተገበራቸው ከሚገኙ ኢኒሼቲቮች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል፣ ኢነርጂ፣ ኢንተርኔት እና የአይሲቲ ፓርኮችን ጨምሮ የመሰረተ ልማቶች አቅርቦት እንዲሁ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የገበያ አቅም እንዳላት አስረድተዋል። ሪች ዲጂታል ምቹ እድሎቹን በመጠቀም በዘርፉ እንዲሰማራ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ተቋም ሪች ዲጂታል (REACH Digital) ተወካዮች በበኩላቸው ተቋሙ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን የማፍሰስ ጠንካራ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ለአይሲቲ ልማት አመቺ ምህዳር እንዳለ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ያለውን ትብብር የማጠናከር ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል -በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
Jan 13, 2025 79
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ከግሉ ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ፈጠራን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶችን ከግሉ ዘርፍ ተቋማት ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱ ከሳይበር ዘብ ኮንሰልቲንግ ፣ከኮርፖ መረጃና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ( ICTET) የዘርፍ ማህበር እንዲሁም ኑና ኢትዮጵያ ከተሰኙ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች ጋር የተከናወነ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ፈጠራ ስራን ለማበረታታት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። የግሉ ዘርፍ ተቋማት የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ፈጠራ ግቦችን ለማሳካት ስምምነቱ የራሱ ፋይዳ አለው ነው ያሉት ሚኒስትሩ። በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ካሉ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ዘላቂ የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ የዘርፉን እድገትን ለማሻሻል እና የማይበገር የኢኖቬሽን ስነ-ምህዳር ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል። ሚኒስትሩ ስምምነቶቹ የግሉ ዘርፍ ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና በፈጠራ ቀጣናዊ መሪ ለመሆን በምታደርገው ጉዞ ውስጥ ጉልህ እርምጃ እንዲኖራቸውና በንቃት እንዲሳተፉ ያስችላቸዋል ማለታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም