ኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ከአፍሪካ ሀገራትና ከአህጉራዊ ተቋማት ጋር ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ ከአፍሪካ ሀገራትና ከአህጉራዊ ተቋማት ጋር ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በክህሎት ልማት ዘርፍ ከአፍሪካ ሀገራትና ከአህጉራዊ ተቋማት ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ዛሬም ቀጥሎ ተካሂዷል።
ከፎረሙ በተጓዳኝ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለወጣቶች የክህሎት ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ አበክራ እየሰራች ትገኛለች።
በአህጉሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራን ተቋማዊ አድርጎ ከመተግበርና አሰራርን ከማመቻቸት አንጻር የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም በክህሎት ልማት፣ በሥራ ገበያና መሰል ጉዳዮች ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ጋር ባለፉት ሶስት ዓመታት በጋራ ስትሰራ ቆይታለች ነው ያሉት።
በዛሬው እለት የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም ከድርጅቱ ጋር የሚሰሩ ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር እና አህጉራዊ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀጣናዊ ጽህፈት ቤት መክፈቱን ገልጸው፤ ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትስስር በማሳደግ በኩል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉዓለም ስዩም በበኩላቸው ተቋሙ በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የስራ እድል ፈጠራን ለማጎልበት እየሰራ ነው ብለዋል።
ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራን ዘላቂነት ባለው መልኩ ለማስፋፋት የሚከናወኑ ስራዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በፋይናንስ ዘርፍና የገበያ ትስስር መፍጠር ስራዎች ላይ የተቀናጀ ድጋፍ በማድረግ የንግድ ድርጅቶችን አቅምና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያደርግም አብራርተዋል።