ብልጽግናን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከጠባቂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ መገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግናን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከጠባቂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ መገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 28/2017(ኢዜአ)፦ብልጽግናን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከጠባቂነት የተላቀቀ አስተሳሰብ መገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "የሚሰሩ እጆች ወግ" የተሰኘ ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል ።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የቦርድ ሰብሳቢና የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ፣ የሃይማኖት አባቶች፡ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ፕሮግራሙ በየ15 ቀኑ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሚቀርብ ሲሆን በስራ ፈጠራ ረገድ ትውልድን የሚቀርጹ ሃሳቦችን የሚያንሸራሽሩበት መሆኑ ተመልክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ከተረጅነት በመላቀቅ ወደ ብልጽግና የሚያደርሱ ትልሞችን ይዘን እየሰራን ነው ብለዋል።
የተያዘው ትልም የሚሳካው ጠንክረን ስንሰራ ብቻ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ለዚህም ሰርተው የተለወጡ አገራት አብነት ሊሆኑን ይገባል ነው ያሉት።
ከስራ ማማረጥና ስንፍና መላቀቅ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ማህበረሰቡ ውስጥ ግንዛቤን የማስፋቱ ጉዳይ አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችን ጨምሮ ትውልድን የሚያንጹ ተቋማት የዜጎችን የስራ ባህል ለመቀየር የሚያስችሉ ግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን አበክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በትምህርት ተቋማትና በስራ ቦታዎችም ዜጎችን የማንቃት ስራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ የስራ ባህልን ለማሳደግ እንደሀገር የማህበረሰብ ምርታማነት ምክክር መርሃ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል ።
የምክክር መርሃ ግብሩ ማህበረሰቡ በየአካባቢው ያለውን ጸጋ በማየትና በመስራት ውጤታማ እንዲሆን በር የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ፕሮግራሙ ለስራ ባህል ማደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ትልቅ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ሰርቶ በመለወጥ ራስን መቻል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የሚሰሩ እጆች ግለሰብንም አገርንም የሚያሳድጉ መንገዶች ናቸው ብለዋል ።
በትኩረት ከተያዘ የስራ ባህል ላይ ተጨባጭ ውጤት እንደሚመጣ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
አገርን ለማሻገር ስራን የማሰቢያ መንገድ፤ ትጋትና ታታሪነትን መርህ በማድረግ ልንረባረብ ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ለ366ሺህ ስራ ፈላጊዎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል ።
የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ስርአት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።