የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ወጣቶች ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መደላድል ይፈጥራል - ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ወጣቶች ለሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መደላድል ይፈጥራል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 4/2017(ኢዜአ)፦ የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ወጣቶች በስራ ዕድል ፈጠራ ያላቸውን ሚና በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መደላድል እንደሚፈጥር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅን በሚመለከት የባለድርሻ አካላት አስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ቤተልሔም ላቀው(ዶ/ር) ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በቋሚ ኮሜቴው የተዘጋጁ ጥያቄዎችን በዝርዝር አቅርበዋል።
በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ አንቀጾች ላይ የሚስተዋሉ የግልጽነትና የትርጓሜ ለውጥ የሚያመጡ ሃሳቦች በድጋሚ ሊፈተሹ እንደሚገባ አንስተዋል።
እንዲሁም የረቂቅ አዋጁን የህግ ማዕቀፍ ዝግጅት፣ የአጋር አካላት ሚና እና የአዋጁን አስፈላጊነት በሚመለከት ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፤ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምላሻቸውም ረቂቅ አዋጁ እንደሀገር የሃብት ምንጭ የሆኑ አዳዲስ አማራጮችንና አሰራሮችን ለማስፋት ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
በዋናነት መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ተግባር ''ከሃሳብ እስከ አምራችነት'' የሚለውን እሳቤ የሚደግፍ መሆኑንም አንስተዋል።
ረቂቅ አዋጁ የወጣቱን አምራችነት ለማሳደግ እንዲያግዝ ታልሞ በጥንቃቄ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው፥ ለዚህም አስቻይ የሆኑ የህግ ማዕቀፎችን ለማካተት ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።
ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን በሚመለከት የሰጠው ግብረ መልስ ጉድለቶችን ለማረምና ለመፈተሽ የሚያግዝ በመሆኑ የቀጣይ የቤት ስራ በማድረግ የመፈተሽ ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ረቂቅ አዋጁ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላትን የማምረት አቅም ለማጉላት እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ያለው አበርክቶ የጎላ መሆኑን ገልጸው፤ በእውቀትና ፈጠራ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ረቂቅ አዋጁን ይበልጥ ለማዳበር ስታርታፖችንና ባለድርሻ አካላትን በቅርበት የማወያየትና ግብዓት የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሰጡት ማጠቃለያ፤ የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ለአካታች ኢኮኖሚ ግንባታ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር አብራርተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ ያላትን የወጣት ኃይል በተገቢው መልኩ ለመጠቀምና የፈጠራ ሃሳብ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የተለያየ የፈጠራ ሃሳብ፣ ችሎታና በቴክኖሎጂ የዳበረ እውቀት ያላቸው ስታርታፖች በመረጡት መስክ ተሰማርተው ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አዋጁ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
የስታርታፕ ረቂቅ አዋጅ ወጣቶች በስራ ዕድል ፈጠራ ያላቸውን ሚና በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ገልጸዋል።