ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር አስደናቂ ነው -የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ተሳታፊ ሚኒስትሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር አስደናቂ ነው -የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ተሳታፊ ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እድገቷን ለማፋጥን በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያከናወነች ያለው ተግባር አስደናቂና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን በ3ኛው የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ተሳታፊ የሆኑ ሚኒስትሮችና የስራ ሃላፊዎች ገለጹ፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የዘርፉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ተሳታፊዎቹ ትናንት ከሰዓት በኋላ የአድዋ ድል መታሰቢያን፣ ሳይንስ ሙዚየምንና የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል የጋና የሠራተኛ፣ ሥራና የሥራ ስምሪት ሚኒስትር አብዱል-ራሺድ ፔልፑዎ ፤ አዲስ አበባ በፈጣን እድገት ላይ መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ እድገቷን ለማፋጠን የጀመረቻቸው ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ ናቸው ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን የሰራተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ጀነራል ጄምስ ሆት ማይ በበኩላቸው በሳይንስ ሙዚየም ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እያከናወነች ያለውን ስራ መመልከታቸውን ነው የተናገሩት።
የተመለከቷቸው ስራዎች ኢትዮጵያ ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግ ዘመናዊ እርሻ ላይ ያላትን ዕቅድ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ተግባራት በአፍሪካ ከምግብ ዋስትና ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን የልማት ስራ እያከናወነች እንደምትገኝ የገለጹት ደግሞ በማላዊ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ልማት ላይ የሚሰራ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ቦንፊስካ ዛሚራ ናቸው።
በሳይንስ ሙዚየም በተመለከቱት ስራ መደነቃቸውን የገለጹት ቦንፊስካ፤ ተግባራቱ ኢትዮጵያን በዘርፉ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ያደርጋታል ብለዋል።