በማዘጋጃ ቤቱ የተጀመረው ዘመናዊ አሰራር መጉላላትን አስቀርቶልናል - የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦ በሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤት በአንድ ማዕከል አገልግሎት የተጀመረው ዘመናዊ አሰራር ሲገጥማቸው የነበረውን መጉላላት እንዳስቀረላቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በበኩሉ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገልጋይ እርካታን ለማምጣት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ አቶ ሰላሙ አኒቶ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በከተማው ማዘጋጃ ቤት ሲሰጥ የነበረው አገልግሎት ያልዘመነ በመሆኑ የተለያዩ ችግሮች ይገጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ቀደም ሲል የመረጃ አያያዙ በወረቀት ብቻ ያተኮረ በመሆኑ የፋይል መጥፋትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች እየተከሰቱ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

መረጃውን ለማፈላለግ በሚባክነው ጊዜና ጉልበት ነዋሪዎች ለእንግልትና ለሙስና ሲዳረጉ መቆየታቸውንም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት በከተማው በቴክኖሎጂ ታግዞ የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከሰው ንክኪ ውጭ መሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ከማስቻሉ ባለፈ ይገጥማቸው የነበረን እንግልት እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።


 

ከዚህ ቀደም አገልግሎት ፈልጎ ወደ ማዘጋጃ ቤቱ የሚመጣ ነዋሪ የራሱን ማህደር እንኳ ለማግኘት መጉላላት ይገጥመው እንደነበር ያስታወሱት ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ክብነሽ ሶዲሶ ናቸው።

በአግባቡ የተሰደረ የመረጃ አያያዝ ስላልነበረ ጉዳይ ለማስፈጸም ለበርካታ ጊዜ በመመላለስ እንጉላላ ነበር ያሉት ነዋሪዋ፣ ለቅሬታቸው በቂ መልስ የሚሰጥ ሰው ባለመኖሩም ጉዳይን ከሙስና ውጭ ለማስጨረስ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

ማዘጋጃ ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዲጂታል የታገዘ ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ፈጣንና ተገቢ አገልግሎት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ መፈጸማቸውን ተናግረው፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን በመፍታት የተጀመረው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማና ኢንደስትሪ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በማዘጋጃ ቤት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በዚህም አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም የሆሳዕና ከተማን ጨምሮ በክልሉ አራት ከተሞች ሙሉ በመሉ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንና ተስፋ ሰጪ ውጤት መታየቱን ተናግረዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡ መዘመኑ ከዚህ ቀደም በተገልጋዮች ላይ ይደርስ የነበረን እንግልትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት እንዳስቻለም ገልጸዋል።

የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትን በማዘመን የተገልጋዩን እንግልት ለመቀነስ የተጀመረው ሥራ በቀጣይም በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ስንታየሁ አስታውቀዋል፡፡

ዘንድሮ በክልሉ በ16 ከተሞች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለህብረተሰቡ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ 

በተለይም መሬትና መሬት ነክ አገልግሎት፣ የግንባታ ፍቃድ እንዲሁም ከልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰበሰብ ክፍያና መሰል አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም