የተቀናጀ የአረምና የተባይ መከላከል ዘዴን ለማስፋፋት እየተሠራ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

አርባምንጭ ፤ሰኔ 27/2017 (ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ የተቀናጀ የአረምና የተባይ መከላከል ዘዴን በማስፋፋት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በተቀናጀ የአረምና የተባይ መከላከያ ዘዴ ዙሪያ በአርባ ምንጭ ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ነው።

በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር) የግብርናው ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተቀናጀ የአረምና የተባይ መከላከያ ዘዴን ለማስፋፋት  እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

ፓርቲኒየም ወይም የቅንጨ አረም በእርሻና በግጦሽ መሬት ላይ በመስፋፋት እንዲሁም ኋይት ስኬል (Mango White scale) የተሰኘው የማንጎ በሽታ በምርትና ምርታማነት ብሎም በእንስሳትና ሰዎች ጤና ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አካባቢን ከሚበክል አሠራር በመውጣት አረምና ተባዮችን በተፈጥሯዊ ወይም ባዮሎጂካል መንገድ ለማስወገድ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ድንበር ዘለል የሆኑ አንበጣ፣ ወፎችና ሌሎች ተባዮችን ለመከላከል የአሰሳና የኬሚካል ርጭት ሥራ የሚያከናውኑ አምስት አይሮፕላኖችን ተገዝተው ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዓለም አቀፍ የስነ-ነፍሳትና ስነ-ምህዳር ምርምር ተቋም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ዕፅዋት ማዕከል የገነባውን ስነ-ህይወታዊ ፀረ-ተባይና ፀረ-አረም ላቦራቶሪ በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል።

ዓለም አቀፍ የስነ-ነፍሳትና ስነ-ምህዳር ምርምር ተቋም ተወካይና ተመራማሪ ሚናሌ ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋሙ የህብረተሰቡን የጤና፣ የሰብል፣ የስነ-ምህዳርና ሌሎች ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ጥናትና ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

ፓርቲኒየም የተሰኘውን አረም ከሌሎች ከሚወገዱ ቁሶች ጋር በማደባለቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል ሥራ ከአርባ ምንጭ ዕፅዋት ማዕከል ጋር መስራቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የማንጎ በሽታን የሚከላከል ነፍሳት ማራቢያ ላቦራቶሪ ገንብተው ለዕፅዋት ማዕከሉ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

በአርባ ምንጭ ዕፅዋት ማዕከል የተገነባው ተባይን በተባይ የመቆጣጠር ዘዴ እንዲሁም በፓርቲኒየም የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ዘዴ ለግብርና ምርታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቆሙት ደግሞ የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ሙላለም መርሻ ናቸው።


 

ቴክኖሎጂው ህብረተሰቡን ከኬሚካል ጥገኝነት የሚያላቅቅ ከመሆኑም በላይ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ፣ ንጹህ አካባቢን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክም ከኬኒያ የመጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት  ጨምሮ የፌዴራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የስነ-ነፍሳትና ስነ-ምህዳር ምርምር ተቋም ተወካዮች፣  ተመራማሪዎች እና ማህበራት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም