የኮደርስ ስልጠና የተሻለ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንድናገኝ መልካም አካጣሚ ፈጥሮልናል - ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
የኮደርስ ስልጠና የተሻለ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንድናገኝ መልካም አካጣሚ ፈጥሮልናል - ወጣቶች

ጂግጂጋ፤ ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና የተሻለ የዲጂታል እውቀትና ክህሎት እንድናገኝ መልካም አካጣሚ ፈጥሮልናል ሲሉ በጂግጂጋ ከተማ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ተናገሩ።
የሶማሌ ክልል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ በበኩሉ በክረምቱ በእረፍት ላይ የሚገኙ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል።
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከወሰዱ ወጣቶች መካከል ሸርማርኬ ሸኪብ አብዲ፤ የስልጠናው እድል በተለይም ለወጣቶች ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ ጥሩ የዲጂታል እውቀት እና ክህሎት እንድንጨብጥ እያደረገን ነው ብሏል።
ከስልጠናው በቀሰመው እውቀት እና ክህሎት በመታገዝ ዌብሳይት በማበልጸግ የራሱን የንግድ ስራ ለማስተዋወቅ እየተጠቀመበት መሆኑን አንስቶ በነፃ እንዲህ አይነት የትምህርት እድል በማግኘቱ አመስግኗል።
የሚገኘው እውቀት ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ተፈላጊ የሚያደርግ መሆኑን አንስቶ ሌሎች ወጣቶችም እድሉ እንዳያመልጣቸው መክሯል።
ሌሎች ስልጠናውን ያገኙት ወጣት አብዲሸኩር መሀመድ አብዲ እና ሰከሪዬ አብዲረህማን ዓሌ፤ የኮደርስ ስልጠናው በብዙ መልኩ ጠቃሚ መሆኑን ካገኘነው እውቀትና ክህሎት ተገንዝበናል ብለዋል።
የአሁኔ ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን የገለጹት ወጣቶቹ መማር፣ መዘጋጀትና ከወቅቱ ጋር መጓዝ የግድ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በተለይም በክረምቱ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ወጣቶች ጊዜያቸውን የኮደርስ ስልጠና በመውሰድ እንዲጠቀሙበት አስገንዝበዋል።
የክልሉ የመረጃ ማዕከል አስተዳደር ዳይሬክተር አብዲአዚዝ አብዲላሂ፤ የኢትዮ ኮደርስ ስለጠና እድሜ ሳይገድበው ለሁሉም ዜጎች በነፃ የሚሰጥ የዲጂታል እውቀት በመሆኑ ሁሉም እድሉን እንዲጠቀምበት መክረዋል።
በተለይም ወጣቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ እውቅት በማዳበር ብቁና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስልጠናው በእጅጉ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ እስካሁን ከ48ሺህ በላይ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸው በክረምቱ በእረፍት ላይ የሚገኙ ወጣቶች ሁሉ የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።