የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል የምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት - ኢዜአ አማርኛ
የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል የምርምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት

አዲስ አበባ፤ሰኔ 27/2017(ኢዜአ)፦የግብርናውን ዘርፍ እድገት ለማስቀጠል የተጀመሩ የምርምር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት ገለፀ።
ኢንስቲትዮቱ በቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ የ2017 አረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቁ ቴክኖሎጂዎችን የሚያሳይ ኤግዚቢሽንም ከፍቷል።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየሰራ ነው።
የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት የማባዛትና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ፣ በአስተራረስና አመራረት ሂደት ዘዴዎች ላይ ክህሎት የማሳደግ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ባሉት 23 ማዕከላት የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ዘርፉን የመደገፍ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤በቀጣይም የግብርናውን እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል።
በኤግዚቢሽኑ የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከልም የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ የሰብልና እንስሳት ዝርያዎችን የማባዛትና ተደራሽ የማድረግ ስራ እያከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ ዛሬ በቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማስጀመሩን አንስተው፤ በ23ቱም ማዕከላት መርሃግብሩ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የቢሾፍቱ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዳኜ ሞጆ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ከ70 ዓመት በላይ በተለያዩ ሰብልና እንስሳት ላይ ምርምር በማድረግ ዝርያዎችን ሲያሻሽል መቆየቱን ገልጸዋል።
ያከናወናቸው ተግባራት ለግብርናው ዘርፍ እድገት አስተዋፅኦ ያላቸው እንደሆኑም ተናግረዋል።
በማዕከሉ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉት የአቮካዶና ፓፓዬ የቡናና ወይራ ችግኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የማዕከሉ የጤና ስፖርት ማህበር ሊቀ መንበር ግዛቸው ካባ እና የሰው ሀብት ክፍል ሰራተኛ የሆኑት ወይዘሮ ድንቅነሽ አየለ፤ ዕጽዋቱ የአካባቢ ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ የሚረዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በመንከባከብ ለፅድቀት ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።