የመጤ የአረም ዛፍ (ፕሮሶፒስ) ወደ ባዮማስ ኃይልነት በመቀየር የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለመቀነስ እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ፣ሰኔ 26/2017 (ኢዜአ) ፦የመጤ የአረም ዛፍን (ፕሮሶፒስ) ወደ ባዮማስ ኃይልነት በመቀየር የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለመቀነስና  የስራ ዕድል ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፕሮሶፒስ ዛፍ የባዮማስ ኃይልን የማምረት የሙከራ ፕሮጀክት እንዲሳካ ግንባር ቀደም ተሳትፎ  ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት በድሬዳዋ ዕውቅናና ሽልማት አበርክቷል።


 

በኢትዮጵያ በጠቅላላው በ2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘው 'ፕሮሶፒስ' የተሰኘው መጤ አረም በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የግጦሽና የእርሻ መሬትን በመውረር ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።


 

ይህንን መጤ አረም በማጨድና በመፍጨት ለኃይል አማራጭነት በማዋል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እንደ ድንጋይ ከሰል በመሆን አገልግሎት እንዲሰጥ ጥናት ሲደረግ ቆይቶ ወደ ተግባር መገባቱ ይታወቃል።


 

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት አለሙ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለሲሚንቶ ምርት ኃይል አቅርቦት የድንጋይ ከሰልን ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።

"ይህን ወጪ ለመቀነስ የ'ፕሮሶፒስ' ዛፍን ወደ ባዮማስ ኃይልነት ለመቀየር የተጀመረው የሙከራ ፕሮጀክት ኃይልን በማምረት ከፍተኛ አቅምን ሊፈጥር ስለሚችል ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲሸጋገር በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ለዚህ የሙከራ ስራ መሳካት ናሽናል ሲሚንቶ ያበረከተው አስተዋጽኦ  በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን አንስተዋል።


 

ለሲሚንቶ ምርት ከውጭ የሚገባን የድንጋይ ከሰልን ምርት መጠን ለመቀነስ መጤ አረሙን ወደ ባዮማስ ኃይልነት በመቀየር የውጭ ምንዛሬን ለመቀነስ እና ለአርብቶ አደሩ የስራ ዕድል ለመፍጠር መሰራቱን አክለዋል።

ሽልማቱ ከተበረከተላቸው መካከል የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ መስራችና ባለቤት አቶ ብዙአየሁ ታደለ በኢትዮጵያ ለሲሚንቶ ማምረቻ በውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን የድንጋይ ከሰል ለመተካት የሚያስችል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ፕሮሶፒስን ወደ ባዮማስ ኃይል  ለመለወጥ ላከናወኑት የሙከራ ፕሮጀክት ዕውቅና  እንደተሰጣቸው ገልፀው ወደ ባዮማስ ኃይልነት ለመለወጥም በግብፅ፣ በአውሮፓና በላቲን አሜሪካ በመዘዋወር ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸዋል።

ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ፕሮጀክቱን ወደ ስራ በማስገባት በናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ የተደረገው የሙከራ ፕሮጀክት ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም  የድንጋይ ከሰልን  በባዮማስ  በመተካት በለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተግባራዊ ለማድረግ  መታቀዱን ጠቁመዋል።

ሌሎች የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የባዮማስ ኃይልን እንዲጠቀሙ ልምዳቸውን ለማካፈልና ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውንም  አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም