3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ አሊ የሱፍ፣የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣የፈጠራ ባለሙያዎች፣ሥራ ፈጣሪዎች እና የዘርፉ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።

ፎረሙ አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር፣ የሥራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ፤ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንና አህጉራዊ ትስስርን ማላቅን ዓላማ አድርጎ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡


 

ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ሲሆን እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

መድረኩ የግብርና እሴት ሰንሰለት፣ዲጂታላይዜሽንና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ በተለይ ለሴቶችና ወጣቶች ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስርን ማላቅ ላይ ያተኮረ ምክክር ይደረግበታል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት፣ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት እና ከአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ ጋር በትብብር ባዘጋጁት በዚህ ፎረም ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ከ1500 በላይ እንግዶች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም