አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም በአህጉሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማስፋት አለብን - የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 1/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም በአህጉሪቷ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር  ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 3ኛው የአፍሪካ የስራ ፈጠራ ፎረም ዛሬም ቀጥሎ ተካሂዷል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ፥ የስራ አጥነት ችግር  የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱ  ፈተና መሆኑን አንስተዋል።

የስራ አጥነት ችግርን ለማቃለል የአፍሪካ አገራት በጋራ በመስራት ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እንደሚችሉ አንስተዋል።

ስለሆነም አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የስራ ፈጠራን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ላይ ትኩረት ተደርጎ መስራት እንደሚገባ  አስታውቀዋል። 

ለዚህም ጥሬ ዕቃ መላክ ብቻ ሳይሆን ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እሴት ጨማሪ የምርት ሰንሰለቶችን በመዘርጋት በዜጋ ተጠቃሚነትና በወጪ ንግድ ዕድገት ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ አካታችነት ስራዎችን በማሻሻልና የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን በመተግበር ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።  

ዜጎች ለህገወጥ ስደት እንዳይዳረጉ፣ በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡና ተከብረው እንዲኖሩ አህጉራዊ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በስራ ገበያ መረጃ ስርዓት፣ በክህሎት መር የስራ እድል ፈጠራ እና በህጋዊ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝም አንስተዋል።

በፎረሙ የፋይናንስ አካታችነት፣ የዲጂታልና የንግድ መሰረተ ልማቶች፣ የህግ ማዕቀፍ ክፍተቶች፣ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም