በዞኑ በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አገልግሎት ለማህበረሰቡ በመስጠት የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በዲጂታላይዜሽን የታገዘ አገልግሎት ለማህበረሰቡ በመስጠት የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል

ደብረ ብርሃን ፤ ሐምሌ 3/2017(ኢዜአ)፦በሰሜን ሸዋ ዞን በዲጂታላይዜሽን የታገዘ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለማህበረሰቡ በመስጠት የተገልጋይን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የሰሜን ሸዋ ዞን የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ በከተሞች የኮሪደር ልማትና በዲጂታላይዜሽን አተገባበር ላይ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በከተሞች ተአማኒነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ዲጂታላይዜሽን የአሰራር ሥርአት እየተዘረጋ ነው።
የዲጂታል አሰራሩ በየደረጃው ያሉ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ ባለፈ ብልሹ አሰራርን ለማስወገድ ያግዛል ብለዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተገልጋይን እርካታ ለመፍጠር ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የኮሪደር ልማትን በማስጀመር የህብረተሰቡን አኗኗር ለማዘመን ትኩረት እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል።
የዞኑ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች ለማዘመን በሚሰራው ሥራም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
በዞኑ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ብርቃብርቅ ተሾመ በበኩላቸው እንዳሉት ከተሞችን ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
ለዚህም በዞኑ ሥር ባለችው የሸዋ ሮቢት ከተማ የኮሪደር ልማት ግንባታ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ቡልጋ፣ አረርቲና ለሚ ከተሞችን ጨምሮ በዞኑ ሥር ባሉ ዘጠኝ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራን ለማስጀመር የሚያስችል የጥናት ሥራ ተጠናቋል ብለዋል።
የአረርቲ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ መሳይ አስታጥቄ በከተማው የኮሪደር ልማት ሥራን ለመጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ልማቱንና የህብረተሰቡን ተሳትፎ በማስመልከት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በስፋት ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
የእንሳሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አከበረኝ ዓለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ተረስተው የቆዩ ከተሞች አሁን ላይ ትኩረት እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ለዚህም የለሚ ከተማ በኢንቨስትመንት እያደገች መምጣቷ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት አቶ አከበረኝ፣ በአዲሱ በጀት ዓመት በከተማው የኮሪደር ልማትና የዲጂታላይዜሽን አሰራርን ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ጠቅስዋል።
በውይይቱ ላይ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።