መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እስከ መስከረም ድረስ 17 እናደርሳለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እስከ መስከረም ድረስ 17 እናደርሳለን - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እስከ መስከረም ድረስ 17 እናደርሳለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሙስናን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እስከ መስከረም ድረስ 17 እናደርሳለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስታዊ ሙስና የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ከአገልግሎት አንጻር ትናንሽ የሙስና ተግባራት አሉ ብለዋል።
ይህን ለማስተካከል ወደ ስራ የገባው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሶስት ወራት ብቻ 23 ተቋማትን በማካተት 124 አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን አንድ ማዕከል ብቻ ነው ያለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ መስከረም ድረስ 17 እናደርሳለን መሶብ እየተስፋፋ አገልግሎት እየዘመነ ሲሄድ የእጅ በእጅ ሙስና እየቀነሰ ይሄዳል ሲሉም አስታውቀዋል።
ከዚያ ውጭ ሙስናን መፀየፍ የግለሰቦችን አመለካከትና ውሳኔን የሚጠይቅ መሆኑንም ማወቅ ይገባል ነው ያሉት።
ሙስናን የምንከላከለው በስርዓት ነው፤ በዘረጋነው የመሶብ ስርዓትም ተገልጋዮች ከ90 በመቶ በላይ እርካታ አሳይተዋል ይህንን በሁሉም አካባቢዎች ማስፋት ከተቻለ ሙስና በእጅጉ ይቀንሳል ብለዋል በማብራሪያቸው።