ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ለሀገራዊ ማንሰራራትና ለዘመናዊ አርበኝነት ስንቅ ነው-ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው 

ባህርዳር፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦የዓድዋ ድል ለሀገራዊ ማንሰራራትና ለዘመናዊ አርበኝነት ስንቅ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ድል ነው

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር 130ኛ ዓመት የዓድዋ ድል በዓልን "የዓድዋ እሴት ለሁለንተናዊ ሀገራዊ ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።


 

በበዓሉ የተገኙት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው፣ የዓድዋ ድል የጀግንነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለትውልዱ አንድነትን፣ ጽናትና ጥንካሬን ያስተማረ ነው ብለዋል።

ድሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ክብር ሲሉ ከሕይወት መስዋዕትነት እስከ አካል መጉደል ዋጋ በመክፈል ሉዓላዊነታቸውን ያጸኑበት የታሪክ አሻራ መሆኑን አንስተዋል።

ልዩነቶችና የግል ፍላጎቶች ከሀገር ሉዓላዊነት በታች መሆናቸውን ያረጋገጠ፣ አርአያነት ያለው የተጋድሎ ስኬት መሆኑንም አመልክተዋል።

የዓድዋ ድል ለሀገራዊ ማንሰራራትና ለዘመናዊ አርበኝነት ስንቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወጣቱ ትውልድ የድሉን ምስጢር በመመርመር አሁን እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች በሀገር ፍቅር ስሜት መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። 


 

ትውልዱ የአባቶቹን የዓድዋ አደራ በማንገብ ለሰላም፣ ለዕድገትና ለሀገራዊ ብልጽግና በአንድነት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በበዓሉ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ገረመው እስከዚያው (ዶ/ር) የዓድዋ ድል በእብሪት የተሞላውን የነጮች የበላይነት የገታ ዓለም አቀፋዊ ክስተት መሆኑን አብራርተዋል። 

ትውልዱ ከበዓል አከባበር ባለፈ የቆራጥነትና የአልገዛም ባይነት ወኔን ተላብሶ በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም