7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሸናፊ የሚሆንበት ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሸናፊ የሚሆንበት ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው - ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሸናፊ የሚሆንበትና የሕዝብ ፍላጎት የሚንጸባረቅበት እንዲሆን በትኩረት እየሰሩ መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።
ቦርዱ ምርጫውን ማካሄድ የሚያስችሉ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ሲሆን የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ያካሂዳል።
ፓርቲዎችም ዕጩዎቻቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን ምርጫ አስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ሥልጠናም በቦርዱ በኩል እየተሰጠ ይገኛል።
በቅርቡ ቦርዱ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት ይፋ ያደረገ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የሥነ ምግባር ደንብም አዘጋጅቷል።
ምርጫውን ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ ለማድረግ ያለመውን የሥነ ምግባር ደንብ ፓርቲዎች ፈርመውታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጥበት እንዲሆን እየሰሩ ነው።
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ሊቀ መንበር ተስፋሁን ዓለምነህ፤ ፓርቲው በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርጫው የሕዝብ ፍላጎት የሚንጸባረቅበት፤ ሕዝብ አሸናፊ የሚሆንበት አካሄድ ተከትለን በምርጫው ለመሳተፍ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ምርጫው በሂደቱም፣ በውጤቱም ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ተዓማኒ መሆን ይኖርበታል ያሉት አቶ ተስፋሁን በዚህ ረገድ ፓርቲያቸው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው በምርጫው መወዳደር የሚያስችለውንና አማራጭ ሀሳብ የያዘውን ፕሮግራም መቅረጹን ጠቅሰው በምርጫው ለዲሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ ተግቶ ይሰራል ብለዋል።
የሲዳማ አንድነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ለማ ኦያቶ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ዕጩዎቹን ማስመዝገቡንና ለፓርቲው አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠቱን አስታውቀዋል።
ምርጫው ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ፓርቲው የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።
የወለኔ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር ፈይሰል አብዲላዚዝ እንደገለጹት፤ ለምርጫው ስኬታማነት የቦርዱን እንዲሁም የሀገሪቱን ሕግ አክብሮ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፓርቲው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ ይፋ ያደረገውን የዕጩዎች የሥነ ምግባር ደንብ መፈረሙን ጨምረው ጠቁመዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች መሰል የሥነ ምግባር መርሆዎችን በመከተልና በመተግበር ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።