ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዘርባጃን ጉብኝት የሁለቱን ሃገራት ትብብር የሚያጠናክር ነው- ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልኡካቸው በአዘርባጃን ያደረጉት የስራ ጉብኝት በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ዘላቂነት የበለጠ የሚያጎለብት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ያደረጉትን የስራ ጉብኝት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ እና አዘርባጃን መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፉት ዓመታት እየተጠናከረ እና የትብብር አድማሱ እየሰፋ እንደሚገኝ በማብራሪያቸው አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪ ደረጃ በአዘርባጃን ጉብኝት ማድረጋቸው እና በተለያዩ መስኮች ስምምነት መፈረማቸው በሀገራቱ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ዘርፈ ብዙና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ድርሻው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሀገራቱ በአዳዲስ ዘርፎች ትብብር ለመፍጠር የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውንም አመልክተዋል።

29ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ(ኮፕ 29) በተሳካ ሁኔታ ያስተናገደችው አዘርባጃን መሰል ዓለም አቀፍ መድረኮችን በማዘጋጀት ጥሩ ልምድ ያዳበረች መሆኑን ገልጸዋል።

አዘርባጃን ይሄንን ልምድ ለማጋራትና አብሮ በትብብር ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዳላት ማሳየቷንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አዘርባጃን ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግቢያ በር አድርጋ እንደምታይና የኢንቨስትመንት እና የንግድ ተደራሽነቷን ለማስፋት እንደምትፈልግ መግለጿን ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ አዘርባጃን የህዝብ አገልግሎቷን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እያከናወነች ያለው ውጤታማ ስራ ልምድ የምትቀስምበት እንደሆነም አንስተዋል።

አጠቃላይ ጉብኝቱ ውጤታማ እንደነበረ እና ለቀጣይ ትብብር ምቹ መደላድል የፈጠረ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም