ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ድል ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢን ድል በማድረግ ለአፍሪካውያን የነፃነት ተስፋን ያበሰረችበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የዩኔስኮ የሰላም ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጋይ ጆከን ገለጹ፡፡

ወጣቶች ከዓድዋ አባቶች የወረሱትን የአይበገሬነት እሴት በልማት መድገም ይጠበቅባቸዋል

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት መንፈስ ቆመው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ያስከበሩበትና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ፋና ወጊ የሆነ ታላቅ ድል ነው።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ለአንድ የጋራ ሀገራዊ ዓላማ በመሰለፍ ሀገሪቱን ለመውረር የመጣውን የጣሊያን ጦር ድል በማድረግ የማይረሳ አኩሪ ገድል የፈጸሙበት ዕለት ነው።

ይህ ታሪካዊ ድል በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "አኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

የዩኔስኮ የሰላም ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጋይ ጆከን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በቅኝ ሊገዛት የመጣውን ኃይል ድል ያደረገች ብቸኛ ሀገር በመሆኗ መላው አፍሪካዊ ሊያውቀውና ሊኮራበት የሚገባ ታሪክ አስመዝግባለች።

የአፍሪካ ሕብረት ምስረታ በአዲስ አበባ መደረጉ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን ኢትዮጵያ በታሪክ ያላት ጉልህ አሻራ ውጤት መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓድዋ ድል ባለፈ በአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ውስጥ በነበራት ንቁ ተሳትፎ ለፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መጎልበት ትልቅ መሠረት የጣለች ሀገር መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡

አፍሪካ የኃያላን አገራትን ትኩረት እየሳበች መምጣቷን አንስተው አህጉሪቱ ያላትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም በዓለም አቀፍ መድረክ ተገቢውን ስፍራ የምትይዝበት ወቅት አሁን እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በልማት ዘርፍ ለአፍሪካ አርአያ በመሆን በኢኮኖሚው መስክ ዳግም ዓድዋን ለመድገም የምታደርገው ጥረት ለአህጉሪቱ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም