የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የጋራ የነፃነት ቀንዲል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የአፍሪካውያን የጋራ የነፃነት ቀንዲል ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የአፍሪካውያን የጋራ ድል መሆኑን የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመከላከያ አመራሮች ገለጹ።
የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት ነው
ሁለተኛው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ኮንፈረንስ “ከአኩሪ ታሪክ፣ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው ላይ የተገኙት ሚኒስትሮችና ወታደራዊ መሪዎች እንዳሉት፤ የዓድዋ ድል ለአህጉራዊ አንድነትና ልማት ትልቅ ትምህርት የሚቀሰምበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአህጉሪቷን ውስብስብ ስትራቴጂካዊ ሁኔታ ለመቋቋም ወታደራዊ ትብብርን ማጠናከር፣ መረጃ መለዋወጥና ጥረቶችን ማቀናጀት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኬንያ መከላከያ ሚኒስትር ሶልፐን ቱያ እንዳሉት፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብ የማንነትና የነፃነት አርማ ነው፡፡
ድሉ በአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ስር ለነበሩ አፍሪካውያን የይቻላል የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀና ለፓን-አፍሪካዊነት እንቅስቃሴ መሠረት የጣለ ታላቅ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።
ዓድዋን ወደ ኋላ የምናይበት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት የምንመለከትበት መነጽር ሊሆን ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ ፤ የዓድዋ ድል መሠረት ጽኑ አንድነትና የማይበገር የሀገር ፍቅር መሆኑን አስገንዝበዋል።
የደቡብ ሱዳን የመከላከያ እና የቀድሞ የጦር አርበኞች ጉዳይ ሚኒስትር ሌተናል ጄነራል ቾል ቶን ባሎክ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከ130 ዓመታት በፊት በዓድዋ የሰው ልጅ እኩልነትን በተግባር ያሳየችበት ነው ብለዋል፡፡
ይህም ለአፍሪካ የነፃነት ንቅናቄ መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያንን መንፈስና ጥንካሬ ዳግም የቀሰቀሰች ታሪካዊ ሀገር መሆኗንም አክለዋል።
የዚምባብዌ የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር ብሪጋዴር ጄኔራል ሌቪ ማዪህሎሜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ድሉን የተቀዳጀችው በማንም ድጋፍ ሳይሆን በአገራዊ አንድነቷ መሆኑ ለሌሎች አገራት ትልቅ ኩራት ነው።
ይህ ነፃነትን በራስ ጥረት ማስጠበቅ ዛሬም ቢሆን ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ለመገንባትና በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት እንደ ትልቅ መነሳሳት እንደሚቆጠር ገልጸዋል።
የዛምቢያ መከላከያ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ጆፍሪ ሲቶንጎ ዚዬሌ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ድሉን ከዘመናዊው የልማት ጉዞ ጋር በማያያዝ እያሳየች ያለችው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በኢነርጂ ዘርፍ መስፋፋት እና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አርአያ መሆኗን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድል ትናንት ነፃነትን እንዳመጣ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ለአፍሪካ ብልጽግና እና ሰላም መከበር እንደ ዋነኛ መነሳሻ ሊያገለግል እንደሚገባ በኮንፈረንሱ ላይ ተመልክቷል።