ቀጥታ፡

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል

ሰመራ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች በንቃት መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለፀ።

ፌዴሬሽኑ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ታዛቢዎችን ለማሰማራት በአፋር ክልል ክላስተር ደረጃ የታዛቢዎች የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናውን ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም እንደተናገሩት ሴቶች በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ሁኖ እንዲጠናቀቅ ሀላፊነታቸው መወጣት አለባቸው።

ሴቷ ለመመረጥም ይሁን ለመምረጥ እንዲሁም በታዛቢነት ተሳትፎዋን ማሳደግ እንድትችል የአሰልጣኞች ስልጠናው ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት ምርጫዎችን በመታዘብና ግንዛቤ በመስጠት የተሳተፈው ፌዴሬሽኑ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድም ሰፋፊ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።

የመራጮችን ግንዛቤ ከማሳደግ አንጻር በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ፋጡማ ሐንፈሬ በበኩላቸው እየተሰጠ ያለው የአሰልጣኞች ስልጠና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚያግዝ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም