ብልፅግና ፓርቲ ዋና መገለጫው ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ውጤት ማስመዝገብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ዋና መገለጫው ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ውጤት ማስመዝገብ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ ዋና መገለጫው ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር በመፈጸም ውጤት ማስመዝገብ ነው ሲሉ በፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ ገለጹ።
ፓርቲው በዘንድሮው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ በንቃት ለመሳተፍ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሕዝብ ድምጽ አሸናፊ የሚሆንበት ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው
ከእነዚህ የዝግጅት ምዕራፎች መካከል አንዱ የሆነውን "ኢትዮጵያ ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሀሳብ የተቀረጸውን ማኒፌስቶውን አስተዋውቋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ ማኒፌስቶው የተዋወቀበት መሪ ሀሳብ ፓርቲው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ከፍታ ለማረጋገጥ ያለውን ፅኑ አቋም ያመለክታል።
ይህም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ በሰው ሀብት ልማት እና በኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ያላትን የመሪነት ሚና ይበልጥ ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት ፓርቲው ለሀገሪቷ የከፍታ ጉዞ ስኬት የነደፋቸውን ሀሳቦችና ፖሊሲዎች ለኢትዮጵያውያን ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል።
የፓርቲው አንዱ መገለጫ ብዝሃነት እና አካታችነት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ማኒፌስቶው በሁሉም መራጭ ዘንድ ተደራሽ እንዲሆን በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲዘጋጅ መደረጉንም አክለዋል።
አቶ መለሰ አያይዘውም ፓርቲው የዘንድሮውን ማኒፌስቶ ሲያስተዋውቅ፣ ካለፈው የምርጫ ወቅት ጀምሮ በተግባር ተፈትኖ ካስመዘገባቸው ተጨባጭ ስኬቶች በመነሳት እንደሆነ አመልክተዋል።
በወቅቱ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለማከናወን ለሕዝብ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች ከግብ ማድረስ መቻሉንም ጠቁመዋል።
ይህ ስኬት ሊመዘገብ የቻለው ከሕዝብ ጋር በትብብርና በመደማመጥ እንዲሁም በጥብቅ የአመራር ክትትል በመሥራቱ መሆኑን አንስተዋል።
ፓርቲው በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን ያቀዳቸውንና ቃል የገባቸውን ተግባራት በውጤታማነት ስለመፈጸማቸው በመስክ ጥናት እና በግምገማ ማረጋገጡን ገልጸዋል።
ለዘንድሮው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የመለየት ሥራ ኢትዮጵያን በሚመስል የአካታችነት መስፈርት መከናወኑን ተናግረዋል።
የዕጩዎች ምዝገባ በዲጂታል ሥርዓት መካሄዱ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰው፤ ፓርቲው የምርጫ ቦርድን አሠራር ተከትሎ በመላ ሀገሪቷ ዕጩዎቹን ማስመዝገቡንም አብራርተዋል።