ምርጫው ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጥሩ መሰረት እንዲያኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫው ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጥሩ መሰረት እንዲያኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት ይገባቸዋል
መቱ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጥሩ መሰረት እንዲያኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት እንደሚገባቸው ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ምልክት ይፋ ያደረገ ሲሆን የምርጫ ሂደቱም ነፃ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲዎች የምርጫ ህጉን አክብረው እንዲሰሩ አስገንዝቧል።
አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱንና የፓርቲዎችን ሃላፊነት በተመለከተ ኢዜአ በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራንን አነጋግሯል።
በዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት ዲን ዩሱፍ ጋዛሊ፤ የምርጫ ዴሞክራሲያዊነት መለኪያው ሂደቱና የፓርቲዎች ሰላማዊና ደሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በቅድመ ምርጫ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን በማክበር የመወዳደሪያ ሐሳባቸውን ለሕዝብ በመሸጥ ተቀባይነት ለማግኘት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ፓርቲዎች የሃሳብና የፖሊሲ ክርክር ላይ ማተኮር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በምርጫው መሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብትና የዜግነት ኃላፊነት በመሆኑ በሂደቱ ለሀገር ሕልውናና ቀጣይነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ግደታ እንዳለባቸውም አንስተዋል።
በመሆኑም የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበትና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ጥሩ መሰረት አኑሮ እንዲያልፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ባሕርይ እና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ መምህር ወንዱ መብራቴ፤ በምርጫው የሚፎካከሩና የሚሳተፉ ሁሉ ከምንም በላይ የሀገርን ሰላምና ህልውና ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ግደታ አለባቸው ብለዋል።
በምርጫው ሂደት ፓርቲዎች በሀሳብ የበላይነት ለመወዳደር ዝግጁ ሆነው አሸናፊ ሃሳብ ይዘው ሊመጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመሆኑም ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲካሄድ የሚፎካከሩ ፓርቲዎችና ደጋፊዎች የየበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።