ዓድዋን ከትናንት አሸናፊነት ባሻገር ለዛሬ ሀገራዊ ግንባታና ለነገ ብሔራዊ ኩራት ልንጠቀመው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋን ከትናንት አሸናፊነት ባሻገር ለዛሬ ሀገራዊ ግንባታና ለነገ ብሔራዊ ኩራት ልንጠቀመው ይገባል
ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ ዓድዋን ከትናንት አሸናፊነት ባሻገር ለዛሬ ሀገራዊ ግንባታና ለነገ ብሔራዊ ኩራት ልንጠቀመው እንደሚገባ ተመላከተ።
ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘው ግብ እውን እንዲሆን ወጣቱ በአርበኝነት ስሜት ሊተጋ ይገባል
የወላይታ ዞን እና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር በጋራ የ130 ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል።
በመድረኩም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በየዘርፉ ለምናስመዘግበው ሁለንተናዊ ልማት የሥነ-ልቦና ስንቅ ይሆናል ብለዋል።
አቶ ተፈሪ አክለውም ዓድዋን ከትናንት አሸናፊነት ባሻገር ለዛሬ ሀገራዊ ግንባታና ለነገ ብሔራዊ ኩራት ልንጠቀመው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶች በዓድዋ ያሳዩትን ገድል የሀገራችንን ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት በማጽናት ሊደግመው ይገባል ብለዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሳሙኤል ተሰማ (ረ/ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል የብዝሃነትና የመቻቻል፣ የፅናትና የቆራጥነት ተምሳሌትና የአንፀባራቂ ጀግንነት ውጤት ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን ወራሪውንና ተስፋፊውን ኃይል ተከላክለው አኩሪ ተጋድሎ ያደረጉበት መሆኑ አውዱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ጀግኖች አባቶቻችን በዓድዋ ተራሮች ባደረጉት ተጋድሎ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጎናጸፈችውን ክብርና ዝና እንደ ወኔ በመታጠቅ ብሔራዊ ጥቅሟን የማስከበር ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የዓድዋ ድል ታሪካዊ ድላችን ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የአብሮነትና የመተባበር ኃይል ምን ያህል ለስኬት እንደሚያበቃ ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም ናቸው።
የዓድዋ ድል አልሸነፍ ባይነት ስነ-ልቦናን የተላበስንበት ድል ነው ያሉት ወይዘሮ እታገኝ የከተማዋ ነዋሪዎችም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ከግብ በማድረስና ለመጪው ትውልድ ውብና ምቹ ከተማን በማውረስ ሊደግሙት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች፣ የሰራዊት አባላት እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።