ቀጥታ፡

ፓርቲዎች ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ምርጫን በሀሳብ የበላይነት ለማሸነፍ የጀመሩት ጥረት መጠናከር አለበት −ምሁራን

ዲላ፤ የካቲት 21/2018(ኢዜአ) ፡-የፖለቲካ ፓርቲዎች ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ በማቅረብና በማስተዋወቅ ምርጫን በሀሳብ የበላይነት ለማሸነፍ የጀመሩት ጥረት የሚበረታታና መጠናከር ያለበት ነው ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ምርጫ ዴሞክራሲ የሚገነባበት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መስፈርት መሆኑን ያነሱት ምሁራኑ ውጤታማ ምርጫ በማካሄድ የሀገርን መልካም ስም ማስቀጠል እንደሚገባም ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ የውስጥ አቅምን በመጠቀም ውጤታማ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ የፖለቲከ ምህዳር በመንግስት ስለመፈጠሩ ጅማሬው እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። 

ፓርቲዎች ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ በማቅረብና በማስተዋወቅ ምርጫን በሃሳብ የበላይነት ለማሸነፍ የጀመሩት ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አንስተው ይህም መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል። 

ምርጫ ዴሞክራሲን ከመገንባት ባለፈ የህዝብ ድምጽ እንዲደመጥ ያደረጋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በሰከነና የምርጫ ህጉን በተከተለ መልኩ የሚደረግ የሀሳብ ሙግትና ፉክክር የተሻለ የፖለቲካ ስርዓት በመገንባት ሀገርን ያጸናል ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መራጩ ህዝብ የሃሳብ የበላይነትን ለድርድር ማቅረብ የለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡   

ምርጫ የዲሞክራሲ ልምድ የሚገነባበት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መስፈርት መሆኑን ያነሱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘርፍ መምህርና ተመራማሪ ደረጄ ክፍሌ (ዶ/ር) ናቸው።

በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ውጤታማ በማድረግ የሃገርን መልካም ስም ለመገንባት ሁሉም የምርጫው ተዋናዮች በሃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ማኒፌስቶና ያሏቸውን አማራጮች ለህዝብ ለማስተዋወቅ የጀመሯቸውን ጥረቶች አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተለይ ፓርቲዎች በሀሳብ የበላይነት ልቆ ለመውጣት ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ተናግረው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከግጭት ቀስቃሽ ንግግርና ተግባር መቆጠብ አለባቸው ብለዋል።

በሀሳብ የበላይነት ምርጫን ለማሸነፍ የሚደረጉ ጥረቶች ዴሞክራሲ እንዲያብብ ሚናው የጎላ በመሆኑ ፓርቲዎችና አባላቶቻቸው በዚህ መልክ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም