ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ሲከበር ለዘላቂ ሰላምና ልማት በበለጠ በመትጋት ሊሆን ይገባል 

ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል ሲከበር ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስመዝገብ የበለጠ በመትጋት ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ 130ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአል ተከብሯል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ፤ የዓድዋን ድል ስናከብር የራሳችንን ታሪክ በመስራት መሆን አለበት ብለዋል።  

በተለይም ሰላምን ዘላቂ ለማድረግና ልማትን ለማስቀጠል የበለጠ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አባቶች በዓድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መትጋት ይገባል

የዓድዋ ድል የተገኘው በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትብብርና አንድነት መሆኑን ጠቁመው በተለይም የቀድሞ አባቶችን ጥበብና ስልት በመላበስ ለልማትና ሰላም መትጋት ይገባል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ሴቶችና ወጣቶች መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ፈንታነሽ አፈወርቅ በበኩላቸው፤ ቀደምት አባቶች በደምና በአጥንታቸው አስከብረዋት ያኖሯትን ሀገር የአሁኑ ትውልድ ከነሙሉ ክብሯ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።


 

ለዚህም ሴቶችና ወጣቶች የልማትና የሰላም ተምሳሌት በመሆን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በሚሰራው ስራ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

ከተሳታፊዎች መካከል ወጣት ህይወት ግዛቸው፤  አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገር ካደጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የበኩላችንን እንወጣለን ብላለች።


 

ዓድዋን ስንዘክር በሰላምና ልማት ስራዎች በበለጠ በመሳተፍ ስኬት ለማስመዝገብ ቃል በመግባት ነው ያለው ደግሞ  ወጣት የሽዋስ ይበልጣል ነው።


 

በበአሉ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አመራር አካላት፣ ወጣቶች ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም