በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች ተመዝግበዋል
ሆሳዕና፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶች መመዝገባቸውን የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ባደረጋቸው ጥረቶች የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ያስቀጥላል
በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የዴሞክራሲ ምህዳርን በማጠናከር አዲሷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ሚናው የጎላ መሆኑም ተመላክቷል።
ብልጽግና ፓርቲ የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ መወዳደሪያ ምልክቱ የሆነውን (የስንዴ ነዶ) እና ማኒፌስቶ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ለህዝብና ለአባላቱ አስተዋውቋል፡፡
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ አኒዮ በዚህ ወቅት እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ በድህነት ቅነሳ ላይ ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።
ፓርቲው የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማቅረብና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጭምር በትብብር በመስራት ስኬት እያስመዘገበ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
በዞኑ በሰላም ግንባታ፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በጤናና በትምህርት ዘርፍ በተከናወኑ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ወጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከድህነት በመውጣት በምግብ ራስን ለመቻል በተተገበሩ የሌማት ትሩፋት መርሀግብርና ሌሎች ኢኒሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በፓርቲው መሪነት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው ያስታወቁት።
በዞኑ በልማትና በመልካም አስተዳደር በተሰሩ ሥራዎች እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የፓርቲው አመራሮችና አባላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሀዲያ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት ግዛው በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግሥት የፖለቲካ ስልጣን ቅቡልነት በህዝብ ድምፅ ብቻ እንዲወሰን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ምህዳር በማጠናከር ለአዲሷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የፓርቲው አባላት ተሳትፈዋል፡፡