ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ለምክክሩ ውጤታማነት መሠረት የሚጥሉ ናቸው - የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ለምክክሩ ውጤታማነት መሠረት የሚጥሉ ናቸው - የፖለቲካ ፓርቲዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት ለምክክሩ ውጤታማነት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ሀገራዊ ምክክሩ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለማዳበር ቁልፍ ሚና ይጫወታል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛው የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የኮሚሽኑን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መገምገሙና ቀሪ ሥራዎችን ለማከናወን የቀረበለትን የጊዜ ማራዘሚያ የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁ ይታወቃል።
በዚህም ለተጨማሪ ስምንት ወራት መራዘሙ የሚታወቅ ሲሆን የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ይህንኑ ውሳኔ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ስራዎች በአግባቡ እንዲያጠናቅቅና አካታችነትን ይበልጥ እንዲያረጋግጥ የስራ ጊዜው መራዘሙ ተገቢ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የምርጫ ኃላፊ አቶ እዮብ መሳፍንት፤ አገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ውጤታማና ትክክለኛ ምክክር እንዲካሄድ ከማድረግ አንጻር የተጨመረው ጊዜ ለምክክሩ ስኬት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራት የሚታዩና ለምክክሩ ውጤታማነት መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ፓርቲያቸው እንደሚያምን ገልጸዋል።
ኢዜማ እስካሁን ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ የኮሚሽኑ ሥራዎች ላይ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ፤ አገራዊ ምክክሩ በዜጎች መካከል ለዘመናት የቆዩ ስብራቶችን ለመጠገን ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ መሆኑን ጠቅሰው የምክር ቤቱ የጊዜ ማራዘሚያ ውሳኔ ቀሪ ሥራዎች በጥራትና በውጤታማነት እንዲከናወኑ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የሁሉንም ዜጎች ድምፅና ተሳትፎ ለማካተት ጊዜ ወስዶ መሥራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
ዜጎች በሂደቱ ላይ የጣሉት ተስፋ እውን እንዲሆን ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎችና የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።