ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክራቸውን የሀገርን ልማትና የህዝብን አብሮነት ማዕከል ባደረገ መልኩ ማካሄድ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የርዕዮተዓለም የምርጫ ክርክራቸውን የሀገርን ልማትና ዕድገት፣ የህዝብን አብሮነት እና መስተጋብር ማዕከል ባደረገ መልኩ ማካሄድ እንደሚኖርባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። 

በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አማራጮች የመወዳደሪያ ምልክትና ማኒፌስቷቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።

ኢትዮጵያውያንም በምርጫው ድምጽ መስጠት የሚችሉበትን ካርድ ለመውሰድና ይበጀኛል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እየተጠባበቁ  ይገኛሉ። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ የሚያቀርቧቸው የምርጫ ቅስቀሳና ክርክሮች ከስሜት ይልቅ ዕውቀትና ምክንያታዊነትን ያስቀደሙ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኅን በኩል በክርክሮች ላይ የሚያቀርቧቸው አማራጭ የፖሊሲ ሀሳቦችና በቀጣይም የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ዜጎች ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።


 

አቶ ከድር ሰኢድ እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የክርክር መድረኮቹ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት አዋጭ የሆኑ ሃሳቦችን ያነገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችን ለይቶ ድምጽ ለመስጠት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

በዘንድሮው ምርጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ክርክር ወቅትም ህዝብን የሚመጥን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ውበት ደጉ በበኩሏ፤ ምርጫ ዜጎች ይበጀኛል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ የሚሰጡበት የአንድ ሀገር የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ ነው ብላለች።


 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክርም የሀገርን ልማትና ዕድገት፣ የህዝብን አብሮነትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ማዕከል ማድረግ እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

ህዝቡም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክርን በመከታተል ሀሳባቸውን ከብሄራዊ ጥቅም አኳያ መፈተሽ እንዳለበት አመልክተው፤ ለሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊነት ገንቢ ሚና መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

አቶ አማን ማሞ በበኩላቸው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ የህዝብን አንድነትና ሰላም ባከበረና በሃሳብ የበላይነት የተመሰረተ መሆን አለበት ብለዋል።


 

ምርጫ የጠንካራ መንግስት ምስረታ፣ የሰላማዊ ፉክክርና የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትዕግስት ማሞ ናቸው።

በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክር ወቅት ዕውቀትና የሀገርን ቀጣይነት የሚያስቀድሙ ሃሳቦችን ለህዝቡ በመሸጥ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

መራጩ ህዝብም ለሀገርና ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይሰራል ይበጃል ለሚለው የፖለቲካ ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት የሚችሉት የምርጫ ክርክሩንና የቅስቀሳ መርሃ ግብሩን ሲከታተሉ መሆኑን ነው የተናገሩት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም