ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በፍቅር ጉልበት የበረቱ ክንዶች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ130ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች የድል አክሊል!
የዓድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው፣ በአንድነት የተሰለፉበትና ድል ያደረጉበት የወል እውነት፣ የወል ክብር፣ የወል ታሪካችን ነው።
ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በፍቅር ጉልበት የበረቱ ክንዶች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው።
ከዓድዋ የምንማረው ታላቅ እውነትና የወል ውርስ አንድ ስንሆን ማሸነፍ እንደምንችል ነው። በዚህ በማይደበዝዝ ዘለዓለማዊ የድል ማኅተም፣ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ ለኛ ዘመን አሸጋግረዋል። በደም በጻፉት ደማቅ የታሪክ ድርሳን ለሀገር ፍቅርና ክብር መሥዋዕት መሆን ምን ማለት እንደሆነም በተግባር አስተምረውናል።
ሀገራችን በልጆቿ ጠንካራ አንድነት አያሌ ፈተናዎችን ተሻግራለች፤ በኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ስንቆም ዓለምን ያስደመሙ ድሎችን መፈጸም እንደምንችልም በተደጋጋሚ አሳይተናል።
ዛሬም ጠንካራና የታፈረች ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባትና ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ገንቢ ሚናችንን መወጣት ይገባናል።
በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ እምቅ ጥበቦች፣ ዕውቀቶችና እሴቶችን በመቀመር ለሀገር የከፍታ ጉዞ ልንጠቀምባቸው ያስፈልጋል።
በወል ጉዳዮች መግባባት ስንፈጥር የሚኖረን የተደመረ ዐቅም፣ ከልዩነት ፖለቲካ ወደ አንድነት፣ ከድህነት ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ ያፋጥነዋል።
ዓድዋ የድል አክሊላችን ነው ስንል፣ ያለፈውን ውድ ታሪካችንን ከዛሬና ከነገ የምንገምድበት ክር፣ በሁሉም መስክ የታፈረችና የኮራች ሀገርን የምንገነባበት ጽኑ መሠረት ስለሆነም ጭምር ነው።