ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለማዳበር ቁልፍ ሚና ይጫወታል

ሰመራ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትና  የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ለማዳበር ቁልፍ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሥራ ዘመን ለስምንት ወራት ማራዘሙ ይታወሳል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በስኬታማነት ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ሚናና ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል

ኮሚሽኑ በእነዚህ ጊዜያት ለማከናወን ከያዛቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል በትግራይ ክልል የምክክር ሂደት ማከናወን፣ እስካሁን የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን በየፈርጁ ለይቶ ማዘጋጀትና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይገኙበታል።

ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የሚሆኑ አወያዮችና አመቻቾችን መለየትና አስፈላጊውን ስልጠና መስጠት፣እንዲሁም ሁሉንም ድምጾች የሚያስተናግድ፣ አሳታፊና አካታች ሀገራዊ የምክክር ጉባኤን ማካሄድ ተጠባቂ ሥራዎች ናቸው።

ከምክክሩ የሚገኙ ውጤቶችን በማጠናቀር የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማዘጋጀትና አፈጻጸማቸውን መከታተል እንዲሁም ሀገር አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማስፋትና የዶክመንቴሽን ሥራዎችን በዘመናዊ የዲጂታል ዘዴ ማደራጀትም ኮሚሽኑ በቀሪ የሥራ ዘመኑ የሚከውናቸው ተግባራት ናቸው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሴት አደረጃጀት የሥራ ሃላፊዎች ሴቶች ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዳይሬክተር ገነት ስዩም እንዳሉት፣ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮች በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ያለውን ሚና በመገንዘብ በምክክር ሂደቱ ከከተማ እስከ ገጠር ያሉ ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉና ፍላጎቶቻቸው በአጀንዳው እንዲካተት መደረጉንም ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፋጡማ ሐንፈሬ በበኩላቸው፣ ፌዴሬሽኑ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሴቶችን መሰረታዊ ችግሮች የመለየትና ዋና ዋና አጀንዳዎችን አደራጅቶ ለኮሚሽኑ የማቅረብ ስራ መሰራቱንም አስታውቀዋል።


 

በሀገራዊ ምክክሩ ሴቶች ተሳታፊ ከመሆን ባለፈ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ሚና ጎልቶ እንዲወጣና በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ፎዚያ አብዱ ናቸው።  

ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም