ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለተተከሉ ችግኞች በተደረገ እንክብካቤ የጽድቀት መጠንን ማሳደግ ተችሏል

ደብረ ማርቆስ ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን ባለፈው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለተተከለው ችግኝ  የእንክብካቤ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት የሚተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን በመጨመር የደን ሽፋኑን ለማሳደግ የእንክብካቤ ስራ እየተሰራ ነው።


 

በዚህም ባሳለፍነው ክረምት ከተተከለው ከ219 ሚሊዮን  በላይ ችግኝ ውስጥ 87 በመቶ የሚሆነው መጽደቅ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት የተመዘገበው የችግኝ ጽድቀት መጠን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሰባት በመቶ በላይ ብልጫ እንዳለው ተመልክቷል።

ከ500 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ችግኞችን በማረም፣ በመኮትኮት፣ ውሃ በማጠጣትና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ በተሰራው ስራ የጽድቀት መጠኑ እንዲጨምር ማስቻሉን ተናግረዋል።

በዞኑ የአነደድ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ስሜነህ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ ልማቱ የተተከሉ ችግኞች የመሬታቸውን ለምነት በመጨመር ምርታማነታቸው እንዲያድግ እያደረገ ነው።

ይሄን በመገንዘብም ዘንድሮ የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ለማድረግ በመጠበቅና በመንከባከብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 


 

የደጀን ወረዳ የሽንቡሪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አንዷለም አምሳሉ በበኩላቸው ፤ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት መጠኑ እንዲጨምር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የተተከሉ ችግኞች የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ማድረጋቸውን ጠቁመው በቀጣይም ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ስራን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሰሩ ተግባራት የዞኑን የደን ሽፋን ባለፈው ዓመት ከነበረበት  ከ17 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 1 በመቶ  ማሳደግ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም