ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጥ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላላት ቁርጠኝነት የተሰጠ ዕውቅና ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጥ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላላት ቁርጠኝነት የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በሚደረግ ሂደት የሚዲያ ሚና ወሳኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ''ውጤታማ የአየር ንብረት ዘገባ፤ ደኅንነቱ ለተረጋገጠ ጠንካራና የተረጋጋ ቀጣና” በሚል መሪ ሃሳብ የ2025 የሚዲያ ሽልማት በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ኢጋድ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለቀጣናዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስም በስትራቴጂክ ዕቅድ መምራት የሚያስችል የማስተባበር ሥራ እየሰራ አንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ በተግባር የተደገፈ ለውጥ አምጪ የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለጎረቤት ሀገራት ጭምር በማጋራት ውጤታማ ስራ ማከናወኗን አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም በአህጉሪቷ የታዳሽ ኃይል መስክ አዲስ ምዕራፍ በመክፈት የዲጂታል ሽግግር አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆን መብቃቱን አንስተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ሌሎች የታዳሽ ሀይል የልማት ስኬቶች ለአፍሪካ የኢንዱስትሪና የዲጂታል ሽግግር በምሳሌነት የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የኢኮኖሚ ግንባታም 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በስኬት በማስተናገድ ቀርጠኝነቷን ለዓለም ማስመስከሯን ገልጸዋል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP 32) በ2027 ለማስተናገድ በሙሉ ድምጽ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ ላላት ቁርጠኝነት የተሰጠ እውቅና መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመዋጋትም መገናኛ ብዙኃን ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸው የኢጋድ 2025 የጋዜጠኞች ዕውቅና ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ እያደገ የመጣው የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች ሽልማት ቀጣናዊ ድምፆችን ለማጉላት ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።

መገናኛ ብዙኃን ሙያተኞችም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ሰላምና ደኅንነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የቀጣናውን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሻሽል ወሳኝ የልማት እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በብራዚል ቤለም በተካሄደው 30ኛ ጉባኤ ላይ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን 32ኛ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP-32) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም