ቀጥታ፡

ፓርኩ በተደረገለት ጥበቃና እንክብካቤ የዱር እንስሳት ቁጥር እየጨመረ ነው 

ገንዳውኃ፣ ሕዳር 17/2018(ኢዜአ)፡ - የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ  በተደረገለት የብዝኃ ህይወት ጥበቃና እንክብካቤ  የዱር እንስሳቱ ቁጥር እየጨመረ  እፅዋቱም እየተስፋፉ መሆኑን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይርጋ ታከለ፤  የፓርኩን ደህንነት ለመጠበቅ በመንግስት እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲያግዙ ከሃይማኖት አባቶችና ከሌሎችም የአካባቢው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር መደረጉን ለኢዜአ ገልጸዋል። 

በዚህም ሕብረተሰቡ ገንዘብና ቁሳቁስ በማዋጣት ጭምር በፓርኩ ውስጥ የስካውት መጠለያ ካምፕና የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ በማከናወን የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህንን ተከትሎም በፓርኩ ውሰጥ የሚገኘው የአጥቢ እንስሳት ዝርያ ቁጥር ከ27 ወደ 30  ሲያድግ  እፅዋቶች  ደግሞ እየተስፋፋ መምጣታቸውን አስረድተዋል። 


 

በተጨማሪም በሕገወጥ አደንና ደን ጭፍጨፋ ተሰደው የነበሩ የዱር እንስሳት እንዲመለሱና በመጥፋት ላይ የነበሩ የእፅዋት ዝርያዎች እንደገና እንዲያገግሙ ማስቻሉንም አንስተዋል። 

ፓርኩ በአብዛኛው የሳር እና ቁጥቋጦ ዝርያ የበዛበት  ቢሆንም  ትላልቅ የደን ዛፎች ባለቤት እንደሆነም በጥናት መለየቱን አስታውቀዋል።  

በፓርኩ ከእንስሳት የቆላ አጋዘን፣ ነብር፣ ጅብ፣ ጉሬዛ ያሉ ሲሆን፤ ከአእዋፋት ደግሞ  ባለነጭ ጀርባ የአፍሪካ ጆፌ አሞራ፣ ቆቅ፣ ዥግራና ሌሎች የዱር እንስሳት፤ እንዲሁም ከደን እፅዋት " ዞቢ ፣ ዲዛ ፣ ኩመር ፣ ወይባ፣ አባሎ፣ ሰርኪን " እና ሌሎችም በፓርኩ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።


 

ይሄን የሀገር ትልቅ ሃብት በሰፊው በማስተዋወቅና ጎብኚዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡ በማድረግ  ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና የአካባቢውን ሕብረተሰብ  ተጠቃሚ ለመድረግ  ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ አምሳሉ ደረጀ በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ በፊት በፓርኩ ክልል ውስጥ የቤት እንስሳት ስምሪት፤ ደን ጭፍጨፋና ሕገወጥ አደን በብዛት ይካሄድ እንደነበር አውስተዋል። 


 

አሁን ፓርኩን መጠበቅ የጽሕፈት ቤቱ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበው ድጋፍ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል። 

ፓርኩ  የሀገር ሀብት ነው፤ ይህን ሀብት በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ደግሞ የእኛ ሃላፊነት ነው ያሉት ደግሞ  አርሶ አደር ደመቀ ሰማ ናቸው። 

በፓርኩ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ግለሰቦች ተይዘው እንዲቀጡ በማድረግ ለፓርኩ ደሕንነት መጠበቅ የድርሻቸውን  እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ እና በመተማ ወረዳ መካከል የሚገኘው  የጎደቤ ብሄራዊ ፓርክ  በጥብቅ ደንነት ከቆየ በኋላ በአማራ ክልል  ምክር ቤት  ደንብ ቁጥር 152/2009 ዓ.ም  ፓርክ ሆኖ  የተቋቋመና 18ሺህ 691 ሄክታር  ስፋት ያለው መሆኑ ተጠቁሟል።

ፓርኩ ከባሕርዳር በ411 ኪሎ ሜትር፣ ከጎንደር ደግሞ በ237ኪሎ ሜትር እንዲሁም  ከዞኑ ማዕከል ገንዳውሃ ከተማ ደግሞ በ133 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም