የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የእንስሳት ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመከላከል በቅንጅት መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የእንስሳት ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመከላከል በቅንጅት መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 21/2018 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የእንስሳት ሃብት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም አፋጣኝና የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ።
ሶስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ሚዲያ አዋርድ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በዚህ መርሃ ግብር ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (pulse of Africa) የሚዲያ አጋር ነው፡፡
የሽልማት ስነ ስርዓት መርሃ ግብር “ውጤታማ የአየር ንብረት ዘገባ ደህንነቱ ለተረጋገጠ፣ ጠንካራ እና የተረጋጋ ቀጣና” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን ነው።
በመርሃ ግብሩ የሁለተኛ ቀን ውሎ "በታላቁ የአፍሪካ ቀንድ በአየር ንብረት መናጋት ዘመን የእንስሳት እርባታ" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
የፓናሉ ተሳታፊዎቹ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰት የተራዘመ ድርቅ ፣ የሙቀት መጨመርና ወረርሽኝ በእንስሳት ሃብት ላይ መጠነ ሰፊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በቀጣናው የምግብ ዋስትናን ላይ ተግዳሮት መደቀኑን ጠቅሰዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ አገሮች የእንስሳት ሃብት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም አፋጣኝና የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች አሳስበዋል።
በኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና አፕሊኬሽኖች ማዕከል የአየር ንብረት ሞዴሊንግ ባለሙያ ታምራት በቀለ (ዶ/ር) ፤ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥና በእንስሳት ጤና ላይ የደቀነውን ስጋት ለመከላከል አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።
በቀጣናው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችሉ መፍትሄዎችን መተግበር ወሳኝ መሆኑንም ባለሙያ ታምራት በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ሙቀትን የሚቋቋም መኖ እና የተሻሻሉና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የእንስሳት ዝርያዎችን ማስተዋወቅ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት ።
በዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ተቋም ከፍተኛ ሳይንቲስት በርናርድ በት በበኩላቸው፤ የክትባት ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፋትና ጠንካራ የበሽታ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመቋቋም ጥናትና ምርምርን ማጠናከር እንደሚገባ የኢጋድ የእንስሳት እርባታ አካባቢዎች እና የእንስሳት ልማት ማዕከል የደረቅ መሬት ልማት ክፍል ኃላፊ ጉያ ሮባ ተናግረዋል።
የአየር ሁኔታ ለውጦችን እና ሊከሰቱ የሚችሉ ድርቆችን አስቀድመው የሚጠቁሙ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።