ቀጥታ፡

በኢሉባቦር ዞን በክረምቱ ወቅት የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ ነው

መቱ ፤ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፡-በኢሉባቦር ዞን በክረምቱ አረንጓዴ አሻራ መርሐግብር የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ በዘመቻ መልክ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የዞኑ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች የተሳተፉበት በክረምቱ ወቅት የተተከሉ ችግኞችን በጋራ እየተንከባከቡ ናቸው።

የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ  በዞኑ በክረምቱ ወራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች  መተከላቸውን አስታውሰዋል።

የችግኞቹን የጽድቀት መጠን ለማሳደግም ህብረተሰቡ እንክብካቤ እንዲያደርግ ግንዛቤ በመፈጠሩ  የዞኑ የመንግስት ሰራኞችን ጨምሮ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ እንክብካቤው በዘመቻ መልክ እየተካሄደ መሆኑን  ጠቁመዋል።

ይህም የጽድቀት መጠናቸው በአሁኑ ወቅት  ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን  ተናግረዋል። 

ለችግኞቹ የሚደረገው እንክብካቤ ጽድቀታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ በአጭር ግዜ ደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው እንዲጎላ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

በችግኝ እንክብካቤው ከተሳተፉ የመንግስት ሰራተኞች መካከል የዞኑ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ባለሞያ  አቶ መላኩ ከበደ  በበኩላቸው  በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በአንድነት የተከልናቸውን ችግኞች በአንድነት የመንከባከብ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

በመንግስት አገልግሎት ለህዝብ ከሚሰጧቸው አገልግሎት ባለፈ  በክረምቱ ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ እንዲጸድቁ ለማድረግ በስፍራው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የተከልሏቸው ችግኞች የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት መትከል ብቻውን  በቂ ባለመሆኑ የእንክብካቤ ስራውን  ማጠናከር  በማስፈለጉ ለዚሁ ተግባር መጥቻለሁ  ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ የሱፍ  ናቸው።

አቶ እንዳሻው ጆቴ በበኩላቸው  የተተከሉ ችግኞችን በጋራ በመንከባከብ ለውጤት  ለማብቃት ያልተቋረጠ ክትትል በማስፈለጉ በተከላ ወቅቱ የገቡትን ቃል  በተግባር ለማዋል ስራው ላይ መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

በክረምቱ  የተተከሉት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ተገቢው እንክብካቤ ካልተደረገላቸው  በመጥፋት  የወጣባቸው  ከፍተኛ ገንዘብ ለብክነት እንደሚዳረግም አክለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም