ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የደመቁበት የኢጋድ የሚዲያ አዋርድ

ሶስተኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ህዳር 20 እና 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የሽልማት ስነ ስርዓቱ “ውጤታማ የአየር ንብረት ዘገባ ደህንነቱ ለተረጋገጠ፣ ጠንካራ እና የተረጋጋ ቀጣና” በሚል መሪ ሀሳብ ተከናውኗል።

ኢጋድ ቀጣናዊ ሁነቱን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ነው።

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ የሽልማት መርሃ ግብሩ የሚዲያ አጋር ሲሆን የሁለት ቀኑን የሽልማት መርሃ ግብር የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠት ለመላው አፍሪካውያን ተደራሽ አድርጓል። የአፍሪካ ኢምፖርት እና ኤክስፖርት ባንክ(አፍሪኤግዚም ባንክ) ለፕሮግራሙ ድጋፍ አድርጓል።

የኢጋድ የሚዲያ አዋርድ ተሳታፊ የሚዲያ ባለሙያዎች ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያን ጎብኝተዋል።

የ2025 የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በ10 ዘርፎች ተከናውኗል።

የህትመት ጋዜጠኝነት፣ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት፣ የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት፣ ዲጂታል ሚዲያ፣ ፎቶግራፈር፣ ሀገር በቀል ዘገባ፣ የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ/ የይዘት ቀራጭ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና የእድሜ ዘመን ሽልማት የሽልማት ዘርፎቹ ናቸው።

400 የሚሆኑ የኢጋድ አባል ሀገራት የሚዲያ ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ያስገቡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 94 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን የሚዲያ ባለሙያዎች መሆናቸውን ኢጋድ አስታውቋል።

ከ94ቱ ኢትዮጵያውያን የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል ሶስቱ በተለያዩ ዘርፎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ጌትነት ሸንቁጤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የ2025 የሚዲያ ሽልማት በዲጂታል ሚዲያ ዘርፍ አሸናፊ በመሆን ሽልማቱን ተቀብሏል።

ጋዜጠኛ ጌትነት ሸንቁጤ ሽልማቱን የተጎናጸፈው “Climate Intelligence for Survival: IGAD’s Push for Accurate, Actionable Data” በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ ነው።

የጋዜጠኛ ጌትነት ጽሁፍ በኢጋድ ቀጣና ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና የሚዳስስ ነው።

በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰት ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋዎችና ኢ-ተገማች የአየር ጸባይ ለውጦች ዜጎችን በማፈናቀል እና በቁም እንስሳት ላይ ያደረሱትን ጉዳት ይቃኛል።

ትክክለኛ፣ ጊዜውን የጠበቀና ለተግባር ምላሽ የሚያገለግሉ የአየር ንብረት መረጃዎች የማይበገር አቅም ለመገንባትና አደጋዎችን ለመከላከል ያላቸውን ሚናም ተዳሷል።

በጽሁፉ ላይ የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያና ትግበራ ማዕከል(ICPAC) የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን በማጠናከር፣ የትንበያ አቅም ማሳደግና የረጅም ጊዜ የአየር ንብረት የመቋቋም አቅም ላይ እያከናወነ ያለው ስራ ተቀምጧል።

የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች፣ የአንበጣ መንጋ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ሌሎች ፈተናዎችን ለመከላከል ተአማኒነት ያለው የአየር ንብረት መረጃ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል።

በተለይም ኑሯቸው በተለያዩ ወቅቶች ላይ ለተመረኮዙ አርሶ እና አርብቶ አደሮች መረጃው ወሳኝ መሆኑን ያስቀምጣል።

ሌላኛው ተሸላሚ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤ) ጋዜጠኛ ሽመክት ጉግሳ ነው። የተሸለመበት ዘርፍ በኦሮምኛ ቋንቋ በሰራው ፕሮግራም ነው።

ፕሮግራሙ ዛፎች ከሰው ህይወት ጋር ያላቸውን ቁርኝት በዋናነት ይቃኛል።

መንደርደሪያውን ከዓለም የዛፍ ጠቀሜታና ጥበቃ በማድረግ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ይዳስሳል።

ዛፍ መትከል ተፈጥሮና የሰው ልጅን እንዴት እንደሚጠብቅ በተቃራኒው መቁረጥ የሚያደርሰውን ጉዳትም ያስቃኛል።

የ21 ደቂቃ ፕሮግራሙ የኦሮሞ ህዝብ በዘመናት መካከል ዛፎችና የደን ሀብቶች እንዲጠበቁ ያደረገው አስተዋጽኦ ተወስቶበታል። በተለይም በገዳ ስርዓት ውስጥ ዛፍን መጠበቅ ያለው ሚና በስፋት ተነስቷል።

አንድ ዛፍ ለአራት ሰዎች መኖር መሠረት ይሆናል፤ ዛፍ መቁረጥ አራት ሰዎችን እንዲሞቱ ያደርጋል የሚል የአባገዳ አስተያየትም ተጠቃሽ ነው።

አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶችና የአካባቢ ማህበረሰቦች ተፈጥሮን ጠብቆ በማቆየት ያላቸው ሚና ቁልፍ እንደሆነ ተመላክቷል።

የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራዲዮ መስራችና ስራ አስኪያጅ አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የህይወት ዘመን ጋዜጠኝነት ሽልማት ተበርክቶላታል።

ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ግንባር ቀደምና በዘርፉ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቷንም ኢጋድ ገልጿል።

በብሮድካስት ሚዲያው ከ40 ዓመት በላይ የቆየችው ጋዜጠኛ መዓዛ ሸገር ኤፍኤም 102.1ን ከ18 ዓመታት በፊት በማቋቋም በኢትዮጵያ ቀዳሚ የመረጃ እና የመዝናኛ ጣቢያ እንዲሆን ማድረጓ አመልክቷል።

ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ አበይት ፕሮግራሞች መካከል “ማንን ምን እንጠይቅልዎ?” እና “ሸገር ካፌ” ተጠቃሽ ናቸው።

ጋዜጠኛዋ በፕሮግራሞቹ ህዝብን ከመንግስት አገልግሎቶች ጋር በማገናኘትና በማህበራዊ፣ የህግ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ላይ የተመረኮዙ ውይይቶች እንዲካሄዱ መድረክ መፍጠር መቻሏንም ነው የገለጸው።

የሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራዲዮ መሪ ሀሳብ በሆነው የእናንተ ሬዲዮ መዓዛ በጋዜጠኝነት ሙያ ህዝብን ለማገልገልና የኢትዮጵያውያንን ድምጽ ለማጉላት ያላትን ቁርጠኝነት ኢጋድ አድንቋል።

ሽልማቱ በቀጣናው ገንቢ ሚና ያለው ጋዜጠኝነት እንዲጎለብት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ኢጋድ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም