ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሰራቻቸው ውጤታማ ሥራዎች የተሰጠ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ነው 

አዲስ አበባ፤ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የኮፕ-32 ጉባኤን እንድታዘጋጅ መመረጧ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሰራቻቸው ውጤታማ ሥራዎች ዳግም የተሰጠ ዓለም አቀፍ ዕውቅና መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ዋና ዋና የዲፕሎማሲ ስራዎችን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ መመረጧ በአረንጓዴ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማበረታቻ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ እና መሰል የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎች ላይ እያከናወነች ለሚገኙ ተግባራት የተሰጠ እውቅና ነው። 

ኢትዮጵያ የኮፕ-32 አስተናጋጅ ሆና መመረጧ በዲፕሎማሲው መድረክ ያላት ተሰሚነት ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ ለመምጣቱ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ-32) ተወካይ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውንም ተናግረዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ አጀንዳዎቿን ለዓለም የምታስተዋውቅበት ትልቅ መድረክ እንደሚሆንም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን-20 ጉባኤ ላይ በመሳተፍ የዲፕሎማሲ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ባደረጉት ንግግር የአፍሪካን ሁነኛ አጀንዳዎችን ማንጸባረቃቸውንም አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተመድ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና ከተለያዩ ሀገራት መሪዎች ጋር ውጤታማ የጎንዮሽ ውይይቶችን ማድረጋቸውንና በርካታ ስምምነቶች መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የማሌዥያና የሲንጋፖር ሀገራት መሪዎች የሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ካላት ሁለገብ የልማት ጉዞ አንፃር ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከሀገራቱ ጋር በነዳጅ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በስማርት ከተማ ልማት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረጉን አስታውቀዋል። 

በተሰሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ምክንያት የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ የከፈቱ ሲሆን፣ ሌሎችም ለመክፈት መወሰናቸው በመግለጫው ተመላክቷል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መስክ የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተም፤ በሳውዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ወደ 23 ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን በቅርቡ ወደ ሀገር መመለስ እንደተቻለ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ በብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት (COP-30) ጉባኤ ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም