ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ሀገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ሀገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው
አዲስ አበባ፤ሕዳር 12/2018(ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ሀገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው ሲሉ የአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ መርሃ-ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለፁ።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬቶችም ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጉልህ ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ ስነ-ምኅዳር ደኅንነት በማስጠበቅ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት (COP-30) ጉባኤ ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት (COP-32) ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጧ ይታወቃል።
አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉትም፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያስገኘ አስደማሚ የልማት ስኬት ተመዝግቧል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬትም 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP-32) ለማስተናገድ ተመራጭ እንድትሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል።
ጉባኤው ላይ የበርካታ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ምክክር በማድረግ ውሳኔ የሚያሳልፉበት መድረክ በመሆኑ ልምድና ተሞክሮን ለመጋራት ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሀገራት በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚያከናወኑት የመሠረተ ልማት ግንባታ ስራና ያስመዘገቡት ስኬት እንደሚታይ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላና የአየር ንብረት ፖሊሲና ስትራቴጂ ትግበራ ያላት ቁርጠኝነት ጉባኤውን ለማስተናገድ ያቀረበችው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረጉን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤና ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ ልምድና አቅም ለመመረጧ ሌላኛው ዐብይ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የፓሪሱን ስምምነት ለመተግበር በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ታሳቢ ያደረጉ የኢትዮጵያ የልማት ተነሳሽነቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርዓያነት የሚወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬቶችም ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አረንጓዴ አሻራ የሥነ-ምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የሥራ ዕድል ፈጠራን በመደገፍ ሂደት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስቀጠል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለአየር ንብረት ተፅዕኖ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታም በ2050 ከካርቦን ልቀት ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የተያዘውን ግብ ዕውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።