በገጠር ክላስተሮች እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር ክላስተሮች እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ ነው
ድሬዳዋ፤ ሕዳር 13/2018(ኢዜአ) ፡- በድሬዳዋ የገጠር ክላስተሮች እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለስነ ምህዳር ጥበቃና ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ገረመው ረጋሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በድሬዳዋ የገጠር ክላስተሮች የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ በስፋት በመከናወን ላይ መሆኑንና በዚህም ውጤት እየመጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በድሬዳዋ የገጠር ክላስተሮች እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለስነ ምህዳር ጥበቃና ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በዘመቻ እና በመደበኛ መርሃ ግብር በተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ በተከናወኑ የልማት ስራዎች ከ60 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል። በዚህም የአካባቢን ስነ ምህዳር ከመጠበቅም ባለፈ ምርታማነትን ማሳደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በቢሮው የህብረት ስራ ማስፋፊያ፣ ግብይትና ግብአት ኤጀንሲ ባለሙያ አቶ ያሲን ኢብራሂም፤ የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢ ስነ ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ የሚታይ ውጤት የመጣበት መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በገጠር አካባቢዎች ምርታማነትን በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑንም አንስተዋል።
በድሬዳዋ የገጠር ክላስተሮች ወጣቶችና ሴቶች ተደራጅተው በሌማት ትሩፋት ኢንሸቲቮች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የለገ ዶል ገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ኢብሳ ሙሳ እና አርሶ አደር አህመድ ዳዌ፤ በአካባቢው የተከናወነው የልማት ስራ በብዙ መልኩ የጠቀማቸውና ውጤትም ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።
የቀበሌው የግብርና ባለሙያ አቶ ምህረት መታዬት፤ አርሶ አደሮቹ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት እርባታ በመሰማራት ስኬታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።