መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉና ለዱር እንስሳት ሀብት የሰጠው ትኩረት ለዱር እንስሳት ጥበቃ ምቹ መደላድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉና ለዱር እንስሳት ሀብት የሰጠው ትኩረት ለዱር እንስሳት ጥበቃ ምቹ መደላድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉና ለዱር እንስሳት ሀብት የሰጠው ትኩረት ለዱር እንስሳት ጥበቃና ባለስልጣኑ ለሚያከናውነው ተግባር ምቹ መደላድል መፍጠሩን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ ገለፁ።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በትናንትናው እለት በለንደን በተካሄደው በአፍሪካ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ የሚሰጠው ፕሪንስ ዊሊያም አዋርድ የ2025 አሸናፊ ሆነዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አሸናፊ የሆኑት ተስክ ጥበቃ ሽልማት 2025 በተዘጋጀው በአፍሪካ በብዝሃ ህይወት ጥበቃ የላቀ ድርሻና አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሰዎች በሚሰጠው የህይወት ዘመን አበርክቶ ሽልማት ዘርፍ ነው።
አቶ ኩመራ በዱር እንስሳት ጥበቃ ዘርፍ ከባለሙያነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ ሲሆን በዘርፉ በተለያዩ የጥናት እና ምርምር እንዲሁም የአስተዳደር ሥራዎች ላይ ያበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ሽልማቱን ለማሸነፍ አስችሏቸዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ እንዳሉት ባለስልጣኑ የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸው በአግባቡ ተጠብቆና ለምቶ በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ይገኛል።
የጥበቃ ቦታዎችን በጥናት ለይቶ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ማቋቋም እንዲሁም የአስተዳደር ስርዓት ዘርግቶ በአግባቡ እንዲጠበቁና እንዲለሙ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለስልጣኑ የዱር እንስሳት መጠለያ፣ የስፖርታዊ አደን የሚካሄድባቸው ጥበቃ ቦታዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምድብ ያሉ የጥበቃ ቦታዎች በአግባቡ እንዲጠበቁ የማድረግ ስራም ያከናውናል ነው ያሉት።
የጥበቃ ስራዎችን ከክልሎች፣ከማህበረሰቡ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ከመስራት ባለፈ በዱር እንስሳት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ከአገራት ጋር በመተባበር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉና ለዱር እንስሳት ሀብት የሰጠው ትኩረት ለዱር እንስሳት ጥበቃና ባለስልጣኑ ለሚያከናውነው ተግባር ምቹ መደላድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ያገኙት ሽልማትም ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አለም አቀፍ እይታ እንዲያገኝ ለማስቻሉ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ሽልማቱ ለዱር እንስሳት ጥበቃ የበለጠ ድምፅ ለመሆን፣ ህፃናት ለተፈጥሮ ሀብት ያላቸውን ተቆርቋሪነት ለማሳደግና የተፈጥሮ ሀብት አርበኛ የሆኑት ሬንጀሮች ማህበር የበለጠ ለማጠናከር እንዲተጉ የቤት ስራ የሚሰጥ ነው ብለዋል።