ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጥ የታዳሽ ኃይል ልማት ቁርጠኝነቷን የሚያረጋግጥ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት(COP-32) ጉባኤ ለማስተናገድ መመረጥ ለታዳሽ ኃይል ልማት ትግበራ ቁርጠኝነቷን የሚያረጋግጥ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በሁሉም የታዳሽ ኃይል አማራጭ ዕምቅ የመልማት አቅም አላት።

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታም የውሃ፣ የፀሐይ፣ የነፋስ፣ ጂኦተርማልና መሰል የኃይል አማራጮች ወሳኝ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን በፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች የፀሐይ ኃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ስኬትም የካርቦን ልቀትና የአየር ንብረት ለውጥ ስጋትን በመቀነስ ዓለም አቀፍ እውቅና እያስቸራት መሆኑን አብራርተዋል።


 

የበለጸጉ ሀገራት ዕድገታቸውን ለማረጋገጥ የተጓዙበት መንገድ በካይ ጋዞችን በመጠቀም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ዓለምን ዋጋ እያስከፈሉ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገነቡ የታዳሽ ኃይል አማራጭ መሠረተ ልማቶችም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየተፈተነ ለሚገኘው ዓለም ከፍተኛ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የታዳሽ ኃይል መሠረተ ልማት ግንባታም የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማት ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በማጠናከር ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎችን የምታስተናግድበትን ዕድል መፍጠሩን አስረድተዋል።

በብራዚል በተካሄደው መድረክ ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባኤን ለማስተናገድ ስትመረጥ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስመዘገበችው ስኬት ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኮፕ-32 ጉባኤን ለማስተናገድ መመረጧ በታዳሽ ኃይል አማራጭ፣ አረንጓዴ ዐሻራ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ላስመዘገበችው ስኬት ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም የኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶችን ደኅንነት በመጠበቅና የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል በመታደግ ወሳኝ ድርሻ እየተጫወተ ነው ብለዋል።

በብራዚል ቤለም በተካሄደው 30ኛ ጉባኤ ላይ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን 32ኛ የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP-32) ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም