ቀጥታ፡

ዝቅተኛ በካይ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 15/2018 (ኢዜአ)፡- በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ዝቅተኛ በካይ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስቴሩ ከፓወር አፍሪካ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ሁለተኛው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2025 ኤግዚቢሽንና ባዛር ከታኅሣሥ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ያካሂዳል፡፡ 

ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ሁለተኛውን ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2025 ኤግዚቢሽንና ባዛር ለማካሄድ በተደረጉ ዝግጅቶችና በሚጠበቁ ውጤቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

ሚኒስትር አለሙ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት መተግበር የጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ መደላድል እየፈጠረ ነው።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ሥራዎች ኢትዮጵያ ኮፕ 32 የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንድታስተናግድ እንድትመረጥ አድርጓታል ሲሉም ጠቅሰዋል።

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍም ታዳሽ ኃይልም ሆነ ዝቅተኛ በካይ ጋዝ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከታኅሣሥ 9 እስከ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ ኤግዚብሽንና ባዛር ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል።


 

በኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ላይ ኤሌክትሪክን ጨምሮ የተለያዩ ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪ አምራቾች፣ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና የጥናትና ምርምር ተቋማት እንደሚሳተፉ አብራርተዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችና መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ በጋራ ውይይት የሚደረግበት መርሐ ግብር መሰናዳቱንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም