ቀጥታ፡

ተቋማት እና ዘርፎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን የውጤት መለኪያቸው ማድረግ አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018(ኢዜአ)፦ እያንዳንዱ ተቋም እና ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን አጠቃቀምን የውጤት እና ግብ መለኪያ በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

“በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የማጠቃለያ ስልጠና በሰጡበት ወቅት ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል አንዱ የዲጂታል ዘርፉን የተመለከተ ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ዘርፉን አስተሳሰሪ አቅም መሆኑን ገልጸው መንግስት የዲጂታል መታወቂያ፣ ሞባይል ባንኪንግ እና ዘመናዊ የክፍያ ዘዴዎች የማስፋት ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ኳንተም ሳይንስ የሰው ልጆች አኗኗር፣ ስራ እና እሳቤ እየየቀሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂን መቀበል አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የኃይልን፣ የምርት እና የተሳትፎ ሕግጋትን እንደገና እየጻፈ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ፋይዳ፣ ፓስፖርት፣ መሶብ፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ዘመናዊ የክፍያ ዘዴ፣ የጉምሩክ እና ገቢዎች ዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት(ኢፍሚስ) በሀገር ውስጥ አቅም እየጎለበተ እና እያደገ መሄድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የተለያዩ ዘርፎች ምን ያህል ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅመዋል? ብለን ከአሁኑ መለካት ካልጀመርን ዘመን መዋጀትን ብንፈልግም አንደርስበትም ነው ያሉት።

ለሁሉም ስራ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የተሟላ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተሳሰር ግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ግቦች በሚል ባነሱት ሀሳብ እያንዳንዱ ከተማ የአንድ መሶብ አገልግሎት መክፈት እንዳለበትም አንስተዋል።

በ100 ፐርሰንት ግቦች ውስጥም የፋይዳ መታወቂያ ሙሉ ለመሉ በኢትዮጵያ መዳረስ እንዳለበት ገልጸው ለዚህም በሁሉም የአስተዳደር መዋቅሮች አበክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ በጣም ወሳኝ ስራ መሆኑን ጠቁመውም ኢኒሼቲቩ መቶ ፐርሰን መሳካት አለበት ብለዋል።

እያንዳንዱ ተቋም እና ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ምን ያህል ተጠቀምኩኝ? በሚል ግብ ማስቀመጥ እንደሚኖርበትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ካላደገ የሚታሰበውን ትራንስፎርሜሽንና ትስስር ማምጣት እንደማይቻልም አመልክተዋል።

በፈጠራ እና ፍጥነት ጥራትንና ብዛትን እውን ለማድረግ መትጋት የመደመር መንግስት ቁልፍ ስራ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም