ቀጥታ፡

የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንግልትን አስቀርቶልናል-  ተገልጋዮች

ባሕር ዳር ፤ ሕዳር 19/2018(ኢዜአ) ፡-  በባሕርዳር ከተማ የተጀመረው መሶብ  የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀደም ሲል  ሲያጋጥማቸው የቆየውን እንግልት በማስቀረት  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተገልጋዮች ገለጹ። 

በአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ለደንበኞች በተሰጠ የአገልግሎት እርካታ 95 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ በተካሄደ ዳሰሳ ጥናት ማረጋገጥ መቻሉም ተገልጿል።


 

በአማራ ክልል ባሕርዳር  መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉዳይ ሲያስፈፅሙ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሃይማኖት ይበልጣል እና  ሰለሞን ውበት በሰጡት አስተያየት፤  በማዕከሉ ከእንግልት ነፃ የሆነ ፈጣን አገልግሎት ማግኘት  እንደቻሉ ተናግረዋል። 

በማዕከሉ ከሰራተኞች አቀባበል ጀምሮ  መልካም የሚባል አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።


 

ቀደም ሲል ማንኛውንም ዓይነት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማት በሚኬድበት ወቅት  ፋይል ጠፋ በሚል ለመፈለግ ቀኑን ሙሉ ማሳለፍ ግድ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ  በዘመናዊ አሰራር ችግሩን በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንደቻሉ አስረድተዋል። 

መሶብ  የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ቀደም ሲል  ሲያጋጥማቸው የቆየውን እንግልት በማስቀረት  ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው  ተገልጋዮቹ ገልጸዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ፤  ሕዝብ የሚቸግራበችውን  አገልግሎቶች በመለየት የማዘመን ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በባሕር ዳር ከተማ የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በ12 ተቋማት 92 አገልግሎቶችን ለመስጠት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ በዘጠኝ ተቋማት 48 አገልግሎቶችን መስጠት እንደተቻለም አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ባንችዓምላክ ገብረማርያም፤ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት አስተዳደር ሪፎርምና የዲጂታል ኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ አካል ሆኖ እየተተገበረ ነው ብለዋል።


 

የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጡ የመንግስትንና የሕዝብን ትስስርን ይበልጥ  በማጠናከር   የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታተ በጥናት ተለይቶ የተገባበት ተግባር መሆኑን አንስተዋል።


 

በክልሉ  አራት የፌደራልና አስር የክልል ተቋማት 54 አገልግሎቶችን እየሰጡ ሲሆን፤  በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ከ10 ሺህ 400 በላይ ደንበኞችን ማስተናገድ እንደተቻለም አስረድተዋል።

ከደንበኞች በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም የአገልግሎት እርካታውን 95 በመቶ ማድረስ መቻሉም ተረጋግጧል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም