ስልጠናው በፈጠራ የታገዘ ተግባራትን ለማከናወን አግዞናል - የኮደርስ ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
ስልጠናው በፈጠራ የታገዘ ተግባራትን ለማከናወን አግዞናል - የኮደርስ ሰልጣኞች
ወልዲያ፤ ሕዳር 19/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የተመቻቸላቸውን ዕድል በመጠቀም በፈጠራ የታገዘ ተግባራትን ለማከናወን እንዳገዛቸው በሰሜን ወሎ ዞን የኮደርስ ሰልጣኞች ገለጹ።
የ "አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ" ስልጠና ኢንሼቲቭ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ የተደረገ የዲጂታል ክሕሎት ማሳደጊያ መረሃ ግብር ነው።
"ትውልድ ይማር፣ ይሰልጥን ፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ
ሲሆኑ፤ ከእነዚህም በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ይገኝበታል።
በሰሜን ወሎ ዞን ባለፉት አራት ወራት ከሁለት ሺህ በላይ ወጣቶችና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮደርስ ስልጠናን በብቃት በማጠናቀቅ የማረጋገጫ ሰርቲፊኬት መውሰዳቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
ስልጠናውን ካጠናቀቁት መካከል የዞኑ የመንግሰት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ባለሙያ የሆኑት ታደሰ አብዬ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ስልጠናው በፈጠራ የታገዘ ተግባራትን ለማከናወን አቅም ፈጥሮልኛል ብለዋል።
በተለይ የኮምፒውተር ስራን አቅልሎ ለመስራትና ከወረቀት የተላቀቀ ዲጂታላይዜሽን አሰራርን መተግበር የሚያስችል እውቀት እንዳገኙበት ተናግረዋል።
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የአገልግሎት አስጣጥን የሚያቀላጥፍ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ሰልጣኝ አቶ ሰለሞን አሰፋ ናቸው።
ስልጠናው ሁለት ወራት እንደወሰደባቸው ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል ያላወቅኳቸውን የመረጃ አያያዝና ሌሎች ዕውቀቶችን እንዳገኝ አግዞኛል ብለዋል።
ስልጠናው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የመልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚያስችል በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድን መሪ አማኑኤል ሮብሶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሕብረተሰቡን በተለይም ወጣቱን በኮደርስ ስልጠና ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
የመርሃ ግብሩ ዓላማ ወጣቱ ትውልድ እንዲሁም አመራሩና ሠራተኛው በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችላቸውን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱም ከ25ሺህ በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በኮደርስ ለማሰልጠን ታቅዶ በተደረገ ጥረት በአራት ወራት ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ማሰልጠን መቻሉን አስታውቀዋል።
በፕሮግራሚንግ ልማት፣ በዳታ ሳይንስ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ ከህሎትን ለማስጨበጥ የተሰጠውን ስልጠና ላጠናቀቁ ሰርትፍኬት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀሪ ወራትም የስልጠና ማዕከላትን በማስፋት የታቀደውን ለማሳካት ሁሉን አቀፍ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ለስልጠናው ስኬት በዞንና በወረዳ የሚገኙ የአይ ሲቲ ማዕከላት፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ አይሲቲ ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑም ተመልክቷል።