ኢትዮ ቴሌኮም ሶስተኛውን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ አገልግሎት አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም ሶስተኛውን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ አገልግሎት አስጀመረ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም ሶስተኛውንና እጅግ ፈጣን የሆነውን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ አገልግሎት በአዲስ አበባ አስጀምሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ሰሚት በተለምዶ ፍየል ቤት አካባቢ ያስገነባውን ሶሰተኛውን ዘመናዊና ፈጣን የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ ጣቢያ አገልግሎት አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት የኢት ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት ጣቢያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መጠቀምን የሚያበረታታና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረው ጥረት አንዱ አካል ነው።
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ከማድረግ በተጨማሪ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ገልፀው፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪ መሙያ ጣቢያ ግንባታ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የባትሪ መሙያ ጣቢያው የተገጠመለት ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና አስተማማኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) ቴክኖሎጂ የባትሪ መስፈርቶችን በመተንተን እንዲሁም የባትሪውን ደህንነት በመፈተሽ የተሽከርካሪውን ባትሪ በፍጥነት ቻርጅ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት ተቋሙ በተከላቸው ሁለት የባትሪ መሙያ ማዕከላት ከ165 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች የኤሌክትሪክ ቻርጅ መጠቀማቸውን ጠቁመዋል።
ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያው በአንድ ጊዜ 16 ተሽከርካሪዎች ባትሪ እንዲሞሉ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው፤ አንድ መኪና በ15 ደቂቃ ባትሪውን መሙላት እንደሚችል ተናግረዋል።