በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ምሕዳሩን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ምሕዳሩን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኢንተርፕርነር ምሕዳሩን ለማስፋት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ።
"በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የኢንተርፕርነርሺፕ ሳምንት ዛሬ ተጠናቋል።
ተቀማጭነቱን አሜሪካን ሀገር ያደረገው ግሎባል ኢንተርፕርነርሺፕ ኔትወርክ፤ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ባዘጋጀቻቸው ኹነቶች ከ200 ሀገራት ጋር ተወዳድራ አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ገልጿል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢንተርፕርነር ምህዳር ግንባታ ላይ የተከናወኑ ስራዎች በዘርፉ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል።
በአሁኑ ወቅት በኢንተርፕርነር ዘርፉ ላይ የተገኘው ስኬት የኢትዮጵያን አዲስ መልክና እድገት ለማስተዋወቅ የሚረዱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ውድድር በማድረግ ከዓለም ስምንተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ በመሆን አጠናቅቃ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በዘንድሮው ዓመትም በርካታ ተቋማት በመደመር እሳቤ በዘርፉ በትብብር መስራታቸው ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ስፍራ በመያዝ ውድድሩን እንድታጠናቅቅ አድርጓል ነው ያሉት።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢንተርፕርነር ዘርፍ ምህዳርን በማስፋት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ተችሏል ያሉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ፤ በቅንጅት ከተሰራ የኢትዮጵያን እድገት ለማሳካት እንደማያዳግትም አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በውድድሩ ያስመዘገበችው ውጤት ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር ችግር ፈቺ ኢንተርፕርነሮችን እና በዘርፉ ምርምር የሚያደርጉ አካላትን ለማፍራት እንደሚረዳ አብራርተዋል፤
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀሰን ሁሴን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዘንድሮው ዓመት ኢንተርፕነር ዘርፉን ለመለወጥ በጋራ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል።
ይህንን ጥረት በማጠናከርም በቀጣይ በተለይ የዘርፉን ምህዳር የማስፋት ስራን ስኬታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም ነው ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ።