ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በአራተኛ መደበኛ ስብሰባው እንዲፈፀሙ ያስቀመጣቸውን ተግባራት አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም አቅጣጫ አስቀምጧል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ተመስገን ጥሩነህ

የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በአራተኛ መደበኛ ስብሰባው እንዲፈፀሙ ያስቀመጣቸውን ተግባራት አፈፃፀም በጥልቀት በመገምገም አቅጣጫ ማስቀመጡን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስተር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የብሔራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በዛሬው ዕለት አምስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ማካሄዱን አስታውቀዋል።

ምክር ቤቱ በአራተኛ መደበኛ ስብሰባው እንዲፈፀሙ ያስቀመጣቸውን ተግባራት አፈፃፀም በጥልቀት በመገምግሞ አቅጣጫ አስቀምጧል ነው ያሉት።

ምክር ቤቱ አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የስራ ክንውን፣ የዲጂታል መታወቂያ የምዝገባ ሂደት እንዲሁም ‘የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደርስ’ ኢኒሼቲቭ ትግበራ አፈጻጸምን ገምግሞ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሷል ሲሉም ገልጸዋል፡፡


 

ከዚህም በተጨማሪ በአገራችን በመከናወን ላይ የሚገኙ እንዲሁም አዳዲስ የዲጂታል ሰራዎች ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጋር ያላቸውን ተጣጣሚነትን በውይይታችን ዳሰናል ብለዋል።

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ረቂቅ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ላይ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኃላ ስትራቴጂ ሰነዱን በማፅደቅ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል ነው ያሉት።

የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታችን በእመርታ የሚያድግበት ዘመን ላይ እንደመሆኑ፤ ምክር ቤቱም ለዚሁ ዕድገት ተገቢውን ሚና ለመወጣት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም